በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የምሥራቅ አፍሪካ ጥምር ጦር በኮንጎ ወሳኝ ከተማን ተቆጣጠረ


በኤም23 ዐማፅያን ከዘጠኝ ወራት በላይ ተይዛ የነበረችውን፣ የምሥራቃዊቷ ዴሞክራቲክ ኮንጎ ወሳኝ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላት ቁልፍ ከተማ - ቡናጋና፣ የምሥራቅ አፍሪካ ጥምር ጦር መልሰው መቆጣጠራቸውን ኃይሉ አስታወቀ።

የጥምር ጦሩ አባል የኾነው የዩጋንዳ ጦር፣ ከተማዋንና አካባቢውን እንደሚቆጣጠርና የኤም23 ዐማፅያን ለቀው የሚወጡበት ጊዜ እንደሚሰጥ፣ የጥምር ጦሩ ቃል አቀባይ ሻለቃ ካቶ ሃሳን ዛሬ አስታውቀዋል፡፡

“የኤም 23 ዐማፂ ኃይል ስለተባበረንና ማለፊያ በመስጠት ከተማዋን እንድንቆጣጠር ስለአደረገ እናመሰግናለን፤” ብለዋል ቃል አቀባዩ፡፡ ኤም23፣ ለዘጠኝ ወራት ይዟት የቆየውን የቡናጋናን ከተማ ስለለቀቀበት ኹኔታ አስተያየት እንዲሰጥ ቢጠይቅም መልስ ማግኘት አለመቻሉን የአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

ዐማፅያኑ ቡናጋናን የመልቀቃቸው አስፈላጊነት፣ በምሥራቅ ኮንጎ ጉዳይ በተከታታይ ሲደረግ በነበረው ድርድር ውስጥ ቁልፍ ጥያቄ እንደነበረ ታውቋል፡፡

ከ120 በላይ የታጠቁ ቡድኖች፥ ለመሬት፣ ለሥልጣንና አንዳንዶቹም ማኅበረሰባቸውን ከጥቃት ለመከላልከል በሚያደርጉት ግጭት፣ ምሥራቅ ኮንጎ ለዓመታት በጸጥታ ዕጦት ስትናጥ ከርማለች፡፡

ኤም23፣ ከዐሥር ዓመታት በፊት፣ ከሩዋንዳ ጋራ የምትዋሰነውን የጎማ ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ ከተጨማሪ እንቅስቃሴዎች ተዐቅቦ በማድረግ፣ ከኹለት ዓመታት በፊት ዳግም ጥቃት በመክፈት በበርካታ ቦታዎችን ይዞታዎቹን አስፋፍቷል፡፡

ሩዋንዳ፣ የኤም23 ዐማፅያንን ትረዳለች፤ የሚል ክሥ፣ በኮንጎ እና በምዕራባውያን ይቀርብባታል፡፡ ሩዋንዳ ግን ክሡን ታስተባብላለች፡፡

XS
SM
MD
LG