በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለምን መጻኢ ያለመረጋጋት እና ረኀብ ለማስቀረት የቢሊዮኖች ድጋፍ ያስፈልጋል - ተመድ


ፋይል - የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሃላፊ ዴቪድ ቤስሊ በሰሜን ኬንያ፣ ዋጋላ መንደር ነዋሪዎች ጋር ተገናኝተው በነበረበት ወቅት - ነሐሴ 19፣2022
ፋይል - የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሃላፊ ዴቪድ ቤስሊ በሰሜን ኬንያ፣ ዋጋላ መንደር ነዋሪዎች ጋር ተገናኝተው በነበረበት ወቅት - ነሐሴ 19፣2022

► “350 ሚሊየን ሰዎችን ለመርዳት 23 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል”

ለረኀብ የተጋለጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመመገብ፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ካልተቻለ፣ በሚቀጥሉት ከ12 እስከ 18 ወራት ውስጥ፣ ዓለም፥ የጅምላ ስደትን፣ መረጋጋት የጎደላቸውን ሀገራት እና በረኀብ የተጠቁ ሕፃናትንና አዋቂዎችን ማየት እንደሚጀምር፣ የኖቤል ተሸላሚው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሓላፊ ዴቪድ ቤስሊ፣ ባለፈው ዐርብ አስጠንቅቀዋል።

ባለፈው ዓመት፣ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከጀርመን የተገኘውን ተጨማሪ ድጋፍ ያደነቁት ዴቪድ ቤስሊ፣ ቻይና፣ የባሕረ ሠላጤው ሀገራት፣ ቢሊየነር ባዕለ ጸጋዎች እና ሌሎችም ሀገራት፣ “ከምንጊዜውም በላይ አሁን ድጋፋቸውን እንዲያፋጥኑ” ሲሉ ጠይቀዋል።

ቤስሊ፣ በዓለም ትልቁ ሰብአዊ ርዳታ ሰጪ በኾነው ተቋም የነበራቸውን ሥልጣን፣ በመጪው ሳምንት የደቡብ ካሮላይና አስተዳዳሪ ለነበሩት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሲንዲ ማኬይን ከማስረከባቸው በፊት በሰጡት ቃለ ምልልስ፣ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ በ49 ሀገራት ውስጥ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልጋቸውን 350 ሚሊዮን ሰዎች ለመርዳት የሚያስፈልገውን፣ 23 ቢሊየን ዶላር ላያገኝ ይችላል፤ የሚለው ስጋት፣ “በከፍተኛ ኹኔታ እንዳስጨነቃቸው” ገልጸዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ የምትሰጠውን የገንዘብ ርዳታ፣ ከ3ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወደ 7ነጥብ 4 ቢሊዮን ማሳደጓንና በተመሳሳይ ጀርመንም፣ ከ350 ሚሊየን ዶላር ወደ 1ነጥብ 7 ቢሊዮን ከፍ ማድረጓን የጠቀሱት ቤስሊ፣ በዓለም ኹለተኛ ትልቁ የኾነውን ኢኮኖሚ የያዘችው ቻይና፣ ባለፈው ዓመት ለተቋሙ የሰጠችው ገንዘብ፣ 11 ሚሊየን ዶላር ብቻ በመኾኑ ድጋፏን እንድታሳድግ ጠይቀዋል።

የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ኹኔታ ከመጨመሩ ጋራ ተያይዞ፣ የባሕረ ሠላጤው ሀገራትም፣ የበለጠ እገዛ ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ያሉት ሓላፊው፣ በተለይ ከምሥራቅ አፍሪካ፣ ከሰሐራ እና ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋራ ግንኙነት ያላቸው የሙስሊም ሀገራት፣ የተሻለ አስተዋፅኦ ማድረግ እንደሚችሉ አስገንዝበዋል፡፡

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተለይ፣ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን፣ በአፍሪካ የሳሕል ክልል የሚገኙ ሀገራትንና ምሥራቅ ሶማሊያን፣ ሰሜናዊ ኬንያን፣ ደቡብ ሱዳንንና ኢትዮጵያን፣ በአጽንዖት ጠቅሰዋል፡፡ የዓለም መሪዎች፣ ከፍተኛ አለመረጋጋት ሊያስከትሉ የሚችሉ የሰብአዊ ርዳታ ክፍተቶች ለአሉባቸው ሀገራት ቅድሚያ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

XS
SM
MD
LG