በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የነቀምት ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሓላፊ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ


የነቀምት ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሓላፊ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:02:13 0:00

የነቀምት ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሓላፊ ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

የነቀምት ከተማ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሓላፊ ደሳለኝ ቦኮንጃ፣ ዛሬ ጠዋት በአልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን፣ የፓርቲው የፖለቲካ ዘርፍ ሓላፊ አቶ ተሰማ ሙለታ፣ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

“አቶ ደሳለኝ፣ በትልቅ አመኔታ እና ተጠያቂነት፣ የተጣለባቸውን ሓላፊነት በኅብረተሰቡ መካከል ሲወጡ የቆዩ ነበሩ። በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ ለኹለት ሰዓት ኻያ ጉዳይ ገደማ፣ ከቤታቸው ወደ ሥራ ቦታቸው ሲያመሩ፣ በማይታወቅ አካል ተመትተው ተሠውተዋል።” ብለዋል።

አያይዘውም “በዚኽ ከተማ ውስጥ በነበረው የጸጥታ ችግር፣ በርካታ ሰዎች መገደላቸው ይታወቃል። አቶ ደሳለኝ በማንና እንዴት ተገደሉ የሚለውን፣ የጸጥታ አካላት ለፍተሻ በመሠማራታቸው እነርሱን ብትጠይቁ የተሻለ ይኾናል።” ብለዋል።

በድርጊቱ ላይ ከከተማው ፖሊስ መምሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። በ33 ዓመት ዕድሜአቸው በታጣቂዎች የተገደሉት የአቶ ደሳለኝ የቀብር ሥነ ሥርዓት፣ ዛሬ ከሰዓት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም፣ የሥራ ባልደረቦቻቸው በተገኙበት፣ በነቀምት ከተማ መፈጸሙን የፖለቲካ ዘርፍ ሓላፊው ገልጸዋል።

ፓርቲው በፌስቡክ ገጹ ላይ በአሰፈረው ጹሑፍ፣ የጽ/ቤቱ ሓላፊ አቶ ደሳለኝ ቦኮንጃ፣ ዛሬ ጠዋት ወደ ቢሯቸው በሚያመሩበት ወቅት በታጠቀ ኃይል በአሠቃቂ ኹኔታ መገደላቸውን አስታውቋል።

የብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሓላፊ አቶ ፈቃዱ ተሰማ፣ ግድያውን የፈጸሙት ከአገሪቱ የለውጥ መንገድ በተፃራሪ የቆሙ አካላት እንደኾኑ ገልጸው፣ ስለ ማንነታቸው በስም ለይተው የጠቀሱት ነገር የለም።

በነቀምት ከተማ እና በሌሎቹም የምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ፣ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ፣ በርካታ የመንግሥት እና የተቋማት የሥራ ሓላፊዎች መገደላቸው ይታወሳል።

ከዚህ ቀደም በተፈጸሙ የሓላፊዎች ግድያዎች፣ መንግሥት “ሸኔ” የሚለውንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀውን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሲወነጅል ቢቆይም፣ ቡድኑ ድርጊቱን አልፈጸምኹም፤ በማለት ሲያስተባብል ቆይቷል።

XS
SM
MD
LG