የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እና የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጥገኝነት ጠያቂዎች የዩኤስ-ካናዳ ድንበርን መደበኛ ባልሆነ መንገድ እንዳያቋርጡ የሚያግድ ስደተኞችን የሚመለከት ስምምነት አርብ ዕለት ይፋ አድርገዋል ።
ፕሬዚደንት ከሆኑ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ካናዳ ያቀኑት ባይደን በቀጠናው ያለውን "በታሪክ ሊጠቀስ የሚችል የስደት ደረጃ " እልባት ለመስጠት ሁለቱ ሀገራት እየሰሩ መሆኑን በኦታዋ በነበረ የሁለትዮሽ የጋዜጠኞች ማስገንዘቢያ ላይ ተናግረዋል ።
ስደተኞችን የሚመለከተው ስምምነት እያንዳንዱ ሀገር ይፋዊ ባልሆኑ ማቋረጫዎች ወደ ድንበሩ የሚደርሱ ጥገኝነት ጠያቂዎችን እንዲመልስ የሚፈቅድ ሲሆን ፣ ካናዳ በየዩናይትድ ስቴትስ በኩል አልፈው ወደ ግዛቶቿ የሚገቡ ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ለመገደብ እንደሚረዳት ተነግሯል ።
በቀደመው ስደተኞችን የሚመለከት ስምምነት የአሜሪካ እና የካናዳ ባለስልጣናት በሁለቱም አቅጣጫዎች በሚገኙ መደበኛ መግቢያ ቦታዎች በኩል የሚመጡ ጥገኝነት ጠያቂዎችን መመለስ ችለዋል።ነገር ግን ይህ አሰራር ኦፊሴላዊ ባልሆኑ መሻገሪያዎች ላይ ሳይተገበር ቆይቷል ።
"ደህንነቱ የተጠበቀ የሶስተኛ ሀገር ስምምነት" ተብሎ በሚጠራው ስምምነት መደበኛ ባልሆኑ መተላላፊያዎች የሚያቋርጡ ስደተኞች ይካተቱ ዘንድ ካናዳ በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ግፊት ስታደርግ ቆይታለች ።