በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሩሲያን እና የቻይናን ፕሮፖጋንዳ ለመቋቋም ስለሚደረግ ጥረት የዩኤስኤጂኤም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናገሩ


የአሜሪካ ድምጽ፤ ዋሺንግተን፣ ዲሲ
የአሜሪካ ድምጽ፤ ዋሺንግተን፣ ዲሲ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ተዓማኒነት ያለው ዜና እንዳይዳረስ አምባገነን መንግሥታት በፈጠሩት ችግር ሳቢያ እርሳቸው የሚመሩት ተቋም “ወሳኝ” ካሉት ጊዜ ላይ መሆኑን የዩናይትድ ስቴትስ ግሎባል ሚዲያ ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አማንዳ ቤኔት ትናንት ሃሙስ ተናገሩ።

ቤኔት ከዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት የበጀት ጉዳዮች አስተዳደር ኮሚቴ ፊት ቀርበው ለህግ አውጭዎች ሲናገሩ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ግሎባል ሚዲያ ኤጀንሲ (ዩኤስኤጂኤም) የዜና አውታሮች ገለልተኛ በሆነ የጋዜጠኝነት ሥራቸው፣ የበለጠ የገንዘብ ድጋፍ ከሚደረግላቸው የሩሲያ እና የቻይና የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት በላቀ ደረጃ ይሰራሉ።” ብለዋል።

"ሩሲያ እና ቻይና የሚመድቡትን የሚመጥን ወጪ ለማውጣት ካልተዘጋጀን በዓለም አቀፉ የመረጃ ጦርነት የመሸነፍ አደጋ ይጠብቀናል።” ብለዋል ቤኔት።

ቤኔት የጋዜጠኝነት ሥራ የጥራት ደረጃ ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት ድርጅታቸው በሥሩ ከሚገኙት የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ተቁማት አንዱ በሆነው የኩባ ብሮድካስቲንግ መሥሪያ ቤት የሳተላይት እና የሥርጭት አፈና በሚደረግበት ጊዜ ያን አልፎ ለማሰራጨት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም እንደ ቻይና እና ኢራን ባሉ አካባቢዎች ተመልካቾቻቸውና አድማጮቻቸውን ለመድረስ ስለሚያደርጉት ጥረት አስረድተዋል። አክለውም ሩሲያ ተዓማኒነት ያለው ዜና ለሕዝብ እንዳይደርስ የምታደርገውን ሙከራ በማለፍ ድርጅታቸው ያለውን ተደራሽነት እና አዎንታዊ ተጽዕኖም አመልክተዋል።

በሌላ ዜና ቤኔት ሥልጣናቸውን እስከለቀቁበት የአውሮፓውያኑ አቆጣጠር 2020 ዓም ድረስ የአሜሪካ ድምጽን በድሬክተርነት የመሩት ቤኔት የሕግ አውጭ አባላት ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ሲሰጡ በድርጅቱ የኤዲቶሪያል ሥራ እና ከማናቸውም የመንግስትም ሆነ የሌሎች ተጽዕኖ የሚከላከለውን አሰራር አክበረው እንደሚሰሩ እና በቅርቡ የአሜሪካ ድምጽ ድርጅታቸውን አስመልክቶ ጽፎት የነበረውን ይዘት ለመቀየር በወሰደው ውሳኔ ድርሻ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በምክር ቤቱ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀ መንበሩ ማይክል ማኩል ከትላን በስቲያ ረቡዕ ለድርጅቱ በጻፉት ደብዳቤ የሥራ ቅጥር አሰራር ሂደቱን አስመልክቶ የአሜሪካ ድምጽ ለንብባ ካበቃው ጽሑፍ ጋር በተያያዘ ዩኤሴጂኤም እና የአሜሪካ ድምጽ ‘ፈጽመዋል’ ያሉት ሳንሱር ጉዳይ እንዳሳሰባቸው ጠቅሰዋል።

"በመንግሥት በጀት እንደሚደገፍ የሚዲያ ተቋም ዩኤስኤጂኤም እና የአሜሪካ ድምጽ እነዚህ ጥብቅ መስፈርቶች ሙሉ በሙሉ

የሚረጋገጡበት፣ ለማንም ያልወገነ አሰራር መሟላት ወሳኝ ነው።” ያሉት ማኩል “ይህም የዩኤሴጂኤም አመራር ከማናቸውም የኤዲቶሪያል ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ውጭ እንዲሆን ማድረግ አስፈላጊ ነው።" ብለዋል።

ጽሑፉ የአሜሪካ ድምጽ በቅርቡ በድርጅቱ የሩሲያ ቋንቋ አገልግሎት ውስጥ የተቀጠሩ ሁለት ጋዜጠኞች ቀደም ሲል በሩሲያ በሚደገፉ የመገናኛ ብዙኃን አውታሮች ውስጥ በሚያገለግሉበት ወቅት በሰሩት ሥራ የተነሳ ከሥራቸው እንዲታገዱ እና ለጊዜው ደመወዝ እየተከፈላቸው እንዲቆዩ መደረጉን ይዘግባል። ጽሁፉ አያይዞም የአሜሪካ ድምጽ የፋርስ አገልግሎት ክፍል ዋና ኃላፊ ሴተራ ደራክሼሽ ሲዬግን ጨምሮ ከቀድሞው አስተዳደር ጋር የነበሩ ውዝግቦችን ይዘረዝራል።

‘ስለራሷ ትክክለኛ ያልሆነ ማስረጃ አቅርባለች፣ የመንግሥት ገንዘብ ተገቢ ላልሆነ ጉዳይ እንዲውል ማድረጓን በምርመራ አረጋግጫለሁ ሲል በቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ አስተዳደር የተሰየመው እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 2020 ላይ ከነበራት የሥራ ኃላፊነት እንድትነሳ አድርጎ ነበር። ሆኖም እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ2021 በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የተሰየመው ዩኤሴጂኤም ያካሄደው ምርመራ ከክሶቹ ነፃ ካደረጋት በኋላ አዲስ የሥራ ኃላፊነት መስጠቱ ይታወሳል።

የቀደመው የድርጅቱ አመራር ያካሄዳቸው የሰራተኞች ምርመራዎች በድርጅቱ የልዩ አማካሪ ቢሮ ዳግም ምርመራ ቢካሄድባቸውም ውጤቶቹ ግን እስካሁን ይፋ አልተደረጉም።

የምክር ቤቱ የበጀት ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ በትናንቱ መደበኛ የምስክሮች ቃል መስሚያ ሥነ ሥርዓት ወቅት የድርጅቱን የመንግስት ገንዘብ አያያዝ አስመልክቶ ማኩል አቅርበውት ለነበረው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም፣ ሲሉ የተወካዮች ምክር ቤት አባሉ ጋይ ሬሸንታለር ወቅሰዋል።

ቤኔት በበኩላቸው ከዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት በኩል ለሚጠበቁባቸው ጥያቄዎች በሙሉ ቢሯቸው ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጠው፤ ‘የማይወዱትን መረጃ ለማስቀረት’ ሲባል የኤዲቶሪያል ሥራ ተላሂዶበታል የተባለውን ጽሁፍ አስመልክቶም በሰጡት አስተያየት “መንግስትንም ሆነ ሌሎች ክፍሎች በጋዜጠኝነት ነጻ አሰራር ላይ ሊያደርጉ የሚችሉትን ተጽዕኖ የሚከላከለው አሰራር መሰረት ጋዜጠኞቻቸው የሚሰሯቸውን ሥራዎች በተመለከተ በሚወስዷቸው ውሳኔዎች ላይ ተጽዕኖ እንዳደርግ አይፈቅድልኝም” ሲሉ መልሰዋል።

የተባለውን ውንጀላ አስመልክቶ ጥያቄ የቀረበላቸው የአሜሪካ ድምጿ ቃል አቀባይ ብርጂት ሰርቻክም በተመሳሳይ የሌሎችን ተጽዕኖ ለመከላከል የቆመው የአሜሪካ ድምጽ ኤዲቶሪያል አሰራር የዩኤሴጂኤም አመራር በዜና አሰራር ሂደት ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ አይፈቅድም።” ሲሉ አስረድተዋል። ጥያቄ የቀረበበት ዜና ዘገባ ማሻሻያ የተደረገበት በተለመደው አሰራር መሰረት፣ የአሜሪካ ድምጽ የዜና ክፍል አዘጋጆች በጽሁፉ ይዘት ላይ የኤዲቶሪያል ግምገማ ካደረጉ በኋላ ነው።” ሲሉም አክለዋል።

የሌሎችን ጣልቃ ገብነት የሚከላከለውን አሰራር “የማይደፈር” ያሉት የዩኤሴጂኤም ቃል አቀባይ በበኩላቸው ‘ድርጅቱ በአሜሪካ ድምጽ ኤዲቶሪያል አሰራር ሂደት ውስጥ እንዳልተሳተፈ ገልጸው ምክር ቤቱ ያቀረበውን ውንጀላ አስተባብለዋል።

“የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኞችም ሆኑ ሌሎች በድርጅታችን ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች ዩኤሴጂኤም የኤዲቶሪያል መመሪያ አልሰጣቸውም። ይህንን ጣልቃ ገብነትን የሚከላከለውን አሰራር እንደተላለፈ አስርጎ ማቅረብም እንደ እውነቱ ትክክል ያልሆነ እና አሳሳች ነው።” ሲሉ ቃል አቀባይዋ በኢሜል በሰጡት ምላሽ አብራርተዋል።

XS
SM
MD
LG