በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቺ ጂንፒንግ ለሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ተመረጡ


የቻይና ፕሬዚዳንት ቺ ጂንፒንግ
የቻይና ፕሬዚዳንት ቺ ጂንፒንግ

የቻይና ፕሬዚዳንት ቺ ጂንፒንግ በሀገሪቱ ምክር ቤት በከፍተኛ ደረጃ በተቀነባበረ ሥነ ሥርዓት ካሁን ቀደም ሆኖ ለማያውቀው ሦስተኛ የሥልጣን ዘመን ተመርጠዋል። በዚህም ቺ በኮሚንስት ፓርቲው እና በሀገሪቱ ላይ ምን ያህል ጠንካራ ሥልጣን እንዳላቸው አሳይተዋል።

ዛሬ አርብ በተካሄደው እና ሌላ ተፎካካሪ ባልቀረበበት የምርጫ ሥነ ሥርዓት የ69 ዓመቱ ቺ የ2952ቱንም አባላት ድምጽ አግኝተው ተመርጠዋል።

በመንግሥቱ ቴሌቭዢን በተላለፈው የምረቃ ሥነ ሥርዓታቸው ላይ ፕሬዚዳንቱ ባደረጉት ንግግር "የበለጸገች፥ ጠንካራ፥ ዲሞክራሲያዊት፥ ዘመናዊ እና ውብ ሶሺያሊስት ሀገር እገነባለሁ" በማለት ቃል ገብተዋል።

ቺ ጂንፒንግ የፕሬዚዳንቶች የሥልጣን ዘመን የሚገድበውን ህግ እአአ በ2018 መሰረዛቸው ይታወሳል። ሆኖም እሳቸው ለሦስተኛ ጊዜ ይመረጡ እንጂ የሌሎች ከፍተኛ የፓርቲው ባለሥልጣናት የሥልጣን ዘመን በሁለት መገደቡ እንዳለ ነው።

በአመዛኙ ምርጫው ለሥነ ሥርዓቱ ሲባል የተደረገም ቢሆን ለሦስተኛ ጊዜ ርዕሰ ብሄር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ሆነው መመረጣቸው ከማኦ ዜዶንግ ወዲህ ጠንካራ ሥልጣን ያላቸው የቻይና መሪ መሆናቸውን አረጋግጠውበታል።

ባለፉት ቅርብ ዓመታት ታማኞቻቸውን ለከፍተኛ የሥልጣን ቦታዎች የሾሙት ፕሬዚዳንቱ ዛሬም ይህንኑ አድርገዋል። ሥራው የታዘዘውን ማጽደቅ የሆነው ፓርላማው የሳቸው አጋር የሆኑትን ዣኦ ሌጂን የምክር ቤቱ ሊቀመንበር ሃን ዤንግን ደግሞ ምክትል ሊቀ መንበር አድርጎ መርጦላቸዋል። በቀጣዮቹ ቀናትም የእርሳቸው ታማኞች ሹመት እንደሚቀጥል ተመልክቷል።

በአውስትሬሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህሩ ዌን ቲ ሱንግ "ጊዜው አሸናፊው ሥልጣን ጠቅልሎ ይያዝ ፖለቲካ ዘመን ነው" ብለው ዋናው ባለድል ቺ ራሳቸው ናቸው ሲሉ አክለዋል።

"ቺ ባሁኑ ሰዓት ባንድ በኩል ያለ ተፎካካሪ የያዙትን ሥልጣን እያጣጣሙ በሌላ በኩል ደግሞ የኋላ ኋላ በሚፈጸሙ ጥፋቶች ሁሉ ተጠያቂው እሳቸው ብቻ እንደሚሆኑ እያሳሰባቸው ሳይሆን አይቀርም" ሲሉ የፖለቲካ ተንታኙ አስረድተዋል።

XS
SM
MD
LG