የአየር ንብረት ለውጥ ተሟጋቾች ዛሬ ቅዳሜ በጀርመን ፓርላማ ህንፃ አቅራቢያ በሚገኝ የሥነ-ጥበት ስራ ላይ ጥቁር ፈሳሽ በመርጨት ተቃውሟቸውን ገልፀዋል። የመብት ተሟጋቾቹ ከሀገሪቱ ህገመንግስት ቁልፍ የሆኑ አንቀፆች የተቀረፀውን ሥነ-ጥበብ ማርከሳቸው ከፓርላማው አፈ ጉባኤ እና ከሌሎች ህግ አውጪዎች ውግዘት አስከትሏል።
ሰልፉን ያዘጋጀውThe Last Generation 'የመጨረሻው ትውልድ' የተሰኘው ቡድን ደጋፊዎቹ በተምሳሌትነት - የጀርመን ሕገ መንግሥት መሠረታዊ መብቶችን የሚገልጹ 19 አንቀጾች የተቀረጹበት ተከታታይ የመስታወት ሰሌዳዎች የውጭ ገፅታ በዘይት መቀባታቸውን ገልጿል።
ቡድኑ ማወጣው መግለጫ "የጀርመን መንግስት መሰረታዊ መብቶቻችንን እየጠበቀ አይደለም" ያለ ሲሆን አሁንም ዘይትን ማቃጠል መብትን ከመጠበቅ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም ሲል ተከራክሯል።
የፓርላማው አፈጉባኤ ባርቤል ባስ ግን የተቃዋሚዎቹ ድርጊት እንዳስደነገጣቸው እና ድርጊቱ "ምንም ሊገባቸው እንዳልቻለ" ገልፀዋል። አፈጉባኤዋ አክለው በእስራኤላዊው አርቲስት ዳኒ ካራቫን የተሰራው እና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኃላ የተዘጋጀው የጀርመን ህገመንግስት ስም እና የተፃፈበት ዓ.ም ተጣምሮ 'ግሩንጅሴትዝ 49' የሚል ስያሜ የተሰጠው የጥበብ ስራ፣ እንደ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የመሰብሰብ የመሳሰሉ መብቶችን ማክበር እና መጠበቅ እንደሚገባ የሚያስታውስ ነው ብለዋል።
የስነጥበብ ስራው ወዲያውኑ እንዲፀዳ መደረጉም ተገልጿል።