በሶማሊላንድ ባለፉት 24 ቀናት በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎችና በጎሳ ሚሊሺያ አባላት መካከል በተደረገ ግጭት 210 የሚሆኑ ሲቪሎች መገደላቸውን አንድ የመንግስት ባለሥልጣን አስታውቀዋል፡፡
በዚሁ ‘ላስ አኖድ’ በተባለችው ከተማ በሚካሄደው ግጭት እስከ አሁን 680 ሰዎች መጎዳታቸውንም የከተማዋ ከንቲባ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
200 ሺህ የሚሆኑ የቤተሰብ አባላት ቤታቸውን ጥለው መሸሻቸውም ታውቋል፡፡
በአካባቢው የሰላም ደሴት ተደርጋ ስትታይ የነበረችው ሶማሊላንድ ባለፉት ሳምንታት ለሶማሊያ ታማኝ በሆኑ ሚሊሺያዎችና በአገሪቱ የጸጥታ ኃይሎች መካከል እየተደረገ ባለ ግጭት ምክንያት ወደለየለት ሁከት ውስጥ ገብታለች፡፡
ላስ አኖድ በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ የምትገኝ ከፊል ራስ ገዝ የሆነችና ወሳኝ የንግድ መሥመር ላይ ያለች ከተማ ስትሆን፣ ሶማሊላንድ እና ፑንትላንድ የይገባልኛል ጥያቄ ያቀርቡባታል፡፡