በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢትዮጵያ በተመድ የሚደረገውን ምርመራ ለማስቆም መሞከሯን ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች ተቃወሙ


ፎቶ ፋይል፦ የተመድ የሰብዊ መብቶች ም/ቤት፣ ጀኒቫ
ፎቶ ፋይል፦ የተመድ የሰብዊ መብቶች ም/ቤት፣ ጀኒቫ

በሰሜን ኢትዮጵያ በተደርገው ጦርነት ወቅት የጦር ወንጀልና ሌሎች ሰቆቃዎች ስለመፈጸማቸው እንዲመረምር የተመደበው ዓለም አቀፍ ገለልተኛ መርማሪ ቡድን ሥራውን እንዲያቋርጥ የሚጠይቀውን የኢትዮጵያ አቋም በመቃወም፣ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ም/ቤት ኢትዮጵያ የምታቀርበውን ሃሳብ ውድቅ እንዲያደርግ 63 የሚሆኑ ዓለም አቀፍ የሲቪልና ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጠይቀዋል፡፡

ድርጅቶቹ በጋራ በጻፉትና በሂውማን ራይትስ ዎች ድህረ ገጽ ላይ የተለቀቀው ደብዳቤ፣ የገለልተኛ መርማሪዎቹ ሥራ ከፍተኛ ዓለም አቀፍ የመብት ጥሰት የተፈጸመባቸው ሰለባዎች ፍትህ እንዲያገኙ ያስችላል፣ በተጨሪም ጦርነቱ በተካሄደባቸው ቦታዎች ነጻ ሚዲያና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በማይገኙበት ሁኔታ የመርማሪው ቡድን ሥራ ወሳኝ ነው ብሏል፡፡

“መንግሥት የፍትህ አካላትን ጨምሮ በሰብዓዊ መብት ጠባቂዎች ላይ እያደረገ ያለው ማዋከብ እጅጉን አሳስቦናል” ብሏል የድርጅቶቹ ደብዳቤ፡፡

“ኢትዮጵያ የገለልተኛ መርማሪዎቹን ሥራ ለማቋረጥ የምታደርገው ሙከራ ከዚህ በፊት ተደርጎ የማያውቅ ሲሆን፣ መንግሥታት ምርመራን ለማስቀረት ም/ቤቱን በሚፈልጉት መንገድ መጠምዘዝ የሚችሉ ሊያስመስል ይችላል” ብሏል የዓለም አቀፍ የሲቪልና ሰብዓዊ መብት ድርጅቶቹ ደብዳቤ፡፡

የሰብዓዊ ም/ቤቱ አባላትና ታዛቢዎች የኢትዮጵያን ሙከራ እንዲያስቆሙና ለገለልተኛ መርማሪዎቹ ያላቸውን ድጋፍ እንዲያረጋግጡ ደብዳቤው ጠይቋል፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ በተደረገው ጦርነት ወቅት የጅምላ ዕልቂት፣ አስገድዶ መድፈርና ካለፍርድ መታሰር የመሰሉ በደሎች ተፈጽመዋል በሚል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እያደረገ ያለውን ምርመራ ለማስቆም የኢትዮጵያ መንግሥት ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ነው ሲል 5 ዲፕሎማቶችን ጠቅሶ ሮይተርስ በትናንትናው ዕለት ዘግቧል።

ይህም የአፍሪካ አገራትንና የምዕራቡን ዓለም ሊከፋፍል ይችላል ሲል ሪፖርቱ ጠቁሟል።

በኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎችና በህወሓት ኃይሎች መካከል ለሁለት ዓመት የተደረገው ጦርነት ባለፈው ጥቅምት በተደረሰ የሰላም ሥምምነት ቢያበቃም፣ ለደረሰው ሰቆቃና በደል አንዱ ሌላውን ተጠያቂ አድርጓል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሲሞቱ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ተፈናቅለዋል።

መሠረቱን በጀኒቫ ያደረገው የተመድ የሰብዊ መብቶች ም/ቤት የሚያደርጋቸውን ምርመራዎች ከዚህ በፊት አቋርጦ ባያውቅም፣ ኢትዮጵያ ም/ቤቱ እያካሄደ ያለውን ምርመራ እንዲያቆም የሚጠይቅ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ በማሠራጨት ላይ ነች።

ሃሳቡ የምርመራ ውጤቱ እንዳይታተምና በምክር ቤቱም ክርክር እንዳይደረግበት የሚጠይቅ ነው ብሏል ሮይተርስ ትናንት በተለይ ባወጣው ልዩ ሪፖርት፡፡

XS
SM
MD
LG