የተኩስ አቁም ሥምምነት ተደጎ የነበረ ቢሆንም፣ የሶማሊላንድ ሠራዊት አባላት ከሚሊሺያ ቡድኖች ጋር ትናንት ማክሰኞ ተጋጭተው እንደነበር የአካባቢው ባለሥልጣናት የሟቾቹን ቁጥር ሳይጠቅሱ ተናግረዋል፡፡
በእአአ 1991 ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ በቀጠናው የሠላም ደሴት ተደርጋ የምትቆጠር ነበረች፡፡
በቅርብ ወራት ውስጥ ግን የፖለቲካ አለመረጋጋት እየታየባት ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ 20 የሚሆኑ ሰዎች በመንግሥት ኃይሎችና በሚሊሺያዎች መካከል ላስ አኖድ በተባለቸው አጨቃጫቂ ከተማ ላይ በተደረገ ግጭት ተገድለዋል፡፡
“የተኩስ ማቆሙን ለማፍረስ በማቀድ የታጠቁ ቡድኖች በሎስ አኖድ በሚገኝ የሶማሊላንድ ብሄራዊ ጦር እዝ ላይ ጥቃት ከፍተዋል” ሲሉ የሶማሊላንድ ባለሥልጣናት ትናንት ማክሰኞ ከሰዋል፡፡
በሎስ አኖድ የሚገኙና አብዲካሪን አሊ ኑር የተባሉ ባህላዊ መሪ ግን በተቃራኒው የሶማሊላንድ ብሄራዊ ጦር አዲስ ጥቃት ከፍቷል ሲሉ መናገራቸውን የኤ.ኤፍ.ፒ ዜና ወኪል ዘግቧል፡፡
አብዛኞቹ ነዋሪዎች አካባቢውን ለቀው መውጣታቸውንና የመብራትና ውሃ እጥረት እንዳለም አሊ ዱክስ አዳ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል፡፡
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዪች ማስተባበሪያ ቢሮ ባለፈው ሣምንት ባወጣው መግለጫ፣ የተኩስ ማቆም ቢታወጅም ከፍተኛ ውጊያ እየቀጠለ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ከ185 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንም ቢሮው ይፋ አድርጓል፡፡