በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ታሊባን የእስላማዊ መንግስት (አይሲስ) አባላትን ገደልኩ አለ


ፋይል - በታሊባን እና እስላማዊ መንግስት መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት በካቡል፣ አፍጋኒስታን ውስጥ የወደመውን ቤት አንድ የታሊባን ተዋጊ ሲፈትሽ ይታያል - ጥር 5፣ 2023
ፋይል - በታሊባን እና እስላማዊ መንግስት መካከል እየተካሄደ ባለው ግጭት በካቡል፣ አፍጋኒስታን ውስጥ የወደመውን ቤት አንድ የታሊባን ተዋጊ ሲፈትሽ ይታያል - ጥር 5፣ 2023

የታሊባን ጸጥታ ኃይሎች አንድ የእስላማዊ መንግስት አባላት መደበቂያን ትናንት ምሽት ወረው በርካታ አባሎቻቸውን መግደላቸውን ባልሥልጣናት አስታውቀዋል።

በእስላማዊ መንግስት አባላት ላይ ተፈጸመ የተባለው ጥቃት የመጣው ሳዑዲ አረቢያ የጸጥታ ችግሮችን በመጥቀስ ዲፕሎማቶቿን ከአፍጋኒስታን ባሰወጣች በሳምንቱ መሆኑ ነው።

የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላ ሙጃሂድ እንዳሉት በጥቃቱ የዳኻሽ ቁልፍ አባላት የተገደሉ ሲሆን ከሟቾቹ ውስጥም የውጪ አገራት ዜጎች ይገኙባቸዋል። ቃል አቀባዩ አያይዘውም ቦታው የዳኻሽ ቡድን ቁልፍ መደበቂያ እንደነበርና በካቡል በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ሲፈጸሙ ለነበሩ ጥቃቶችና ወንጀሎች ተጠያቂ እንደነበር ተናግረዋል። የቃል አቀባዩን ክስ ግን በገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አለመቻሉን የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ አያዝ ጉል ከኢስላማባድ በላከው ዘገባ አመልክቷል።

በአፍጋኒስታን የሚንቀሳቀሰው የእስልምና መንግስት ቡድን ባለፉት ወራት የሩሲያና ፓኪስታን ኤምባሲዎችን እንዲሁም በቻይኖች የሚተዳደር ሆቴልን ኢላማ ያደረጉና በርካታ ህይወት የቀጠፉ የቦምብ ጥቃቶችን ፈጽሟል ተብሏል።

አንድ አጥፍቶ ጠፊ የሽብር ቡድኑ ዓባል ባለፈው መስከረም በሩሲያ ኤምባሲ ደጃፍ ላይ ራሱ ላይ በማፈንዳት ሁለት የኤምባሲው ሰራተኞችንና አራት ቪዛ ለመጠየቅ የመጡ አፍጋኒስታውያንን ገድሏል። በታህሣስ ወር ደግሞ የፓኪስታን ዲፕሎማቲክ ቡድን መሪ ከግድያ ሙከራ ለጥቂት አምልጠዋል።

አሜሪካ የታሊባንን መግለጫዎች በጥርጣሬ የምትመለከት ሲሆን፣ በአካባቢው የሚቀሳቀሰውን የእስልምና መንግስት ቅርንጫፍ ቡድንን ግን ዋሽንግተን “አደገኛ” ስትል ትገልጸዋለች።

XS
SM
MD
LG