በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰልፉን ማራዘሟን አስታወቀች


ፎቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ማኅበራዊ ገፅ የተገኘ።
ፎቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ማኅበራዊ ገፅ የተገኘ።

- “መንግሥት የገባውን ቃል የማይፈጽም ከኾነ መንፈሳዊ ተጋድሏችን ይቀጥላል፤”/ቅዱስ ሲኖዶስ/

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለነገ እሑድ፣ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠርቶት የነበረውን ሰልፍ ለሌላ ጊዜ ማራዘሙን ገለጸ። ሰልፉ የተራዘመው መንግሥት የጥያቄዎቹን ተገቢነት አምኖበት ምላሽ ለመስጠት በመስማማቱ እንደ ኾነ ቅዱስ ሲኖዶሱ በመግለጫው አስታውቋል።

ቅዱስ ሲኖዶሱ ዛሬ ቀትር ላይ በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ፣ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የተመራው የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዑክ፣ ትላንት የካቲት 3 ቀን 2015 ዓ.ም. ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋራ ባደረገው ውይይት ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በተጨማሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሚኒስትሮች እና የሀገር ሽማግሌዎች በተገኙበት በተካሔደው በዚኹ ውይይት፣ “መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን አቋም መቀበሉን” ቅዱስ ሲኖዶሱ ገልጿል።

መግለጫውን በንባብ ለብዙኀን መገናኛዎች ያሰሙት የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ጸሐፊ አቡነ ጴጥሮስ፣ “ቤተ ክርስቲያን ከሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ እና አስተዳደራዊ ሕጓ ውጭ ምንም ዐይነት ድርድር እንደማታደርግ” በውይይቱ ላይ መግለጿን ተናግረዋል፡፡
ይህን መሠረት በማድረግ፣ “መንግሥትም የቤተ ክርስቲያንን አቋም በመቀበል ወደፊትም የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እና ሉዓላዊነት በጠበቀ መንገድ እንደሚሠራ አረጋግጧል፤” ብለዋል፡፡

የቤተ ክርስቲያኒቱን ቀኖና በመጣስ የኤጲስ ቆጶስነት ሹመት የተፈጸመላቸው አካላት ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ይዞታዎች በኀይል ለመግባት ከአደረጉት እንቅስቃሴ ጋራ በተያያዘ በተፈጠረው ግጭት ለተከሠተው ሞት እና ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች ተጠያቂ የሚኾኑ አካላትን ለሕግ ለማቅረብ እንዲሁም፣ ሕጋዊ እና ተቋማዊ መብቷን መጋፋቱ በአስቸኳይ እንዲቆም፣ በእስር ላይ የሚገኙም እንዲፈቱ ከስምምነት መደረሱ ተገልጿል፡፡

በመኾኑም፣ ቅዱስ ሲኖዶስ ለነገ እሑድ፣ የካቲት አምስት ቀን የጠራውን ሰልፍ ለተወሰነ ጊዜ ማራዘሙን በዛሬው መግለጫው አመልክቷል፡፡

በሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ጠርቶት የነበረው ሰልፍ ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ የተወሰነው፣ የአቋም ለውጥ በማድረግ ሳይኾን፣ ቤተ ክርስቲያን በአስተላለፈችው ጥሪ እና በአስቀመጠችው ቀነ ገደብ መሠረት፣ በመንግሥት በኩል ችግሩን ወዲያውኑ ለመፍታት ፍላጎት በማሳየቱ ምክንያት ብቻ ነው፤” ያለው ቅዱስ ሲኖዶሱ፣ ነገር ግን “መንግሥት የገባውን ቃል እና የወሰነውን ውሳኔ የማይፈጽም ከኾነ መንፈሳዊ ተጋድሏችን ይቀጥላል፤” ብሏል፡፡

የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ እንዳይካሔድ መንግሥት ከትላንት በስቲያ የሰጠውን መግለጫ ተከትሎ፣ የክልል መንግሥታትም ባወጡት መግለጫ፣ ለሰልፉ እውቅና እንደማይሰጡና ማስጠንቀቂያውን ችላ በማለት ሰልፍ የሚካሔድ ከኾነ ርምጃ እንደሚወስዱ በየበኩላቸው አስጠንቅቀው ነበር፡፡ኾኖም ቤተ ክርስቲያኒቱ፣ የካተት ኹለት ቀን በሰጠችው መግለጫ፣ ጥያቄዋ በኹለት ቀናት ውስጥ ምላሽ ካላገኘ፣ የጠራችው ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚካሔድ በድጋሚ መግለጿ ይታወሳል፡፡

ይህን መግለጫ ተከትሎ በቀጣዩ ቀን፣ ማለትም ትላንት የካቲት 3 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የእንነጋገር ጥሪ እንዳቀረቡ ያስታወቀው የቤተ ክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በዛሬው መግለጫው፣ “መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን ጥሪ ተቀብሎ የውይይት መድረክ በማዘጋጀት የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንደሚፈጸም ማረጋገጡን” ጠቅሶ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ተወካዮች እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መካከል የተደረገውን ውይይት እና የተደረሰውን ስምምነት በተመለከተ ከመንግሥት በኩል እስከ አሁን የተባለ ነገር የለም፡፡

በተመሳሳይ፣ ራሱን “የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” በማለት የሚጠራው አካል፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጋራ በተመሳሳይ ቀን የጠራውን ሰልፍ ለሌላ ጊዜ ማራዘሙን ትላንት መግለጹ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ሥልጣነ ክህነታቸውን አስሬና ማዕርገ ጵጵስናቸውን ሽሬ ለይቻቸዋለኹ ያለቻቸው አባ ሳዊሮስ፣ በሀገር ውስጥ ለሚገኝ ብዙኀን መገናኛ በሰጡት መግለጫ፣ የተጀመረውን የዕርቀ ሰላም ሒደት እንደሚደግፉ ገልጸዋል፡፡

በቤተክርስቲያኗ የተፈጠረው ችግር አሁን ያለበት ደረጃ ላይ የደረሰው፣ ባለፈው ወር ጥር 14/2015 ዓ.ም. በደቡብ ምእራብ ሽዋ ሀገር ስብከት በሶዶ ዳጩ ወረዳ ሐሮ ባለወልድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ፣ ሦስት አባቶች ማለትም አባ ሳዊሮስ፣ አባ ኤዎስጣቴዎስ እና አባ ዜና ማርቆስ፣ 26 ኢጲስ ቆጶሳትን ሾመናል ማለታቸውን ተከትሎ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያን፣ ድርጊቱ ሕገ ወጥ መኾኑን ጠቅሳ፣ ሹመት ሰጡ የተባሉትንና ሹመቱን የተቀበሉ አባቶችን አውግዛ መለየቷ ይታወሳል፡፡ ይኹን እንጂ፣ በቤተ ክርስቲያን ከሀብት ክፍፍል እና በቋንቋ ከመገልገል ጋራ በተያያዘ ችግሮች እንዳሉ የሚገልጸውና ራሱን “የኦሮሚያ እና የብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” ብሎ የሚጠራው አካል፣ የወሰደው ርምጃ ሕጋዊ እና ተገቢ እንደኾነ በመግለጽ ይሞግታል፡፡

የዚሁ ቡድን አባላት የኾኑ አባቶች፣ በኦሮሚያ ክልል ወደሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች፣ መንበረ ጵጵስናዎች እና አብያተ ክርስቲያናት ሲገባ፣ ይህን በመቃወም በወጡ ምእመናን እና በጸጥታ ኃይሎች መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወቃል።
በተለይ በሻሸመኔ የሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲኾን፣ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ቢያንስ ስምንት ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጫለኹ፤ ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በሕገ ወጥነት ለአወገዘችው አካል ድጋፍ ያደርጋል በማለት መንግሥትን ስትከስ፣ መንግሥት በበኩሉ፣ ከኹለቱም አካላት ገለልተኛ ነኝ፤ ችግራቸውን በውስጥ አሠራር ይፍቱ፤ ማለቱ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ፣ ኢሰመኮ እና ኢሰመጉ በአወጧቸው መግለጫዎች፣ መንግሥት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሕገ ወጥነት የተፈረጀውን አካል ወግኖ በጸጥታ ኀይሉ አማካይነት(በተለይ በኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ኃይል) ከመጠን ያለፈ ርምጃ መውሰዱን አመልክተዋል፡፡
በቤተ ክርስቲያኗ ከተፈጠረው ችግር ጋራ በተያያዘ ስለ ደረሰው ጉዳት፣ በመንግሥት በኩል እስከ አሁን የተባለ ነገር የለም፡፡

XS
SM
MD
LG