በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኤርትራ ወታደሮች “ትግራይ ውስጥ የመብት ረገጣ ፈጽመዋል የሚባለው የፈጠራ ወሬ ነው” ፕሬዚዳንት ኢሳያስ


ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ

የኤርትራ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ጦርነት ትግራይ ክልል ውስጥ የመብት ረገጣዎችን ፈጽመዋል የሚሉት ውንጀላዎች ከቅዠት የሚቆጠሩ ናቸው ሲሉ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ተናገሩ፡፡

የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በዛሬው የኬንያ ጉብኝታቸው ላይ የሀገራቸውን ወታደሮች ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘት በተመለከተ ጋዜጠኞች ለሰነዘሩላቸው ጥያቄዎች በቀጥታ መልስ ሳይሰጡ “ይሄ የፈጠራ ወሬ ፋብሪካዎች የምላቸው ጭንቅላታቸው ውስጥ የሚፈጥሩት ነው”ብለዋል፡፡

የኤርትራ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለኢትዮጵያ መንግሥት ኃይሎች ጎን ሆነው የተዋጉ ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ እና የመብት ቡድኖች በጦርነቱ አስከፊ የጭካኔ አድራጎቶች በመፈጸም ወንጅለዋቸዋል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማቆም ባለፈው ህዳር ወር የሰላም ሥምምነት የተፈረመ ሲሆን ኤርትራ በሥምምነቱ አልተካፈለችም፡፡

የኤርትራን ወታደሮች ትግራይ ውስጥ መኖር በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥያቄ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በሰጡት መልስ “የኢትዮጵያን የሰላም ሂደት ለማደናቀፍ እና ኢትዮጵያን እና ኤርትራን ለማጋጨት ሀሰተኛ መረጃ የማሰራጨት ዘመቻው ቢቀጥልም በዚህ ጉዳይ ውስጥ ለመግባት ፍላጎት የለኝም” ብለዋል፡፡

አክለውም “ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በአጠቃላይ በቀጣናው ላሉ ችግሮች ኤርትራን ምክንያት አታድርጉ፡፡ እኛን ጎትታችሁ ልትከትቱን አትሞክሩ፡፡ ይሄ የሰላም ሂደቱ ግቡን እንዳይመታ ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ወገኖች ቅዠት ነው” ብለዋል፡፡

የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገባው አክሎም ከዓለም እጅግ አምባ ገነን መንግሥታት አንዷ የሆነችው ኤርትራ የኢትዮጵያን መንግሥት ለመደገፍ ወታደሮቿን ወደትግራይ መላኳን እና በብዙ መቶዎች የተቆጠሩ ሲቪሎችን በመግደል የቀረበባትን ውንጀላ ተከትሎ ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ እንደጣለችባት አመልክቷል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ሀገራቸው የኢጋድ ማለት የምስራቅ አፍሪካ ሀገሮች የልማት በይነ መንግሥታት አባልነቷን ለማደስ መወሰኗን አስታውቀዋል፡፡

የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው ኤርትራ በቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋት ስለምትጫወተው ሚና እንዲሁም የሶማሊያን ብሄራዊ የጦር ሰራዊት ለመገንባት ስላበረከቷቸው አስተዋጽዖ አሞግሰዋል፡፡

የኬንያው ፕሬዚዳንት አክለውም ሀገራቸው በአስመራ ኢምባሲ እንደምትከፍት አስታውቀዋል፡፡ ሁለቱ ሀገሮች በተጨማሪም ኬንያውያን እና ኤርትራውያን ከዛሬ እአአ የካቲት 9/2023 ጀምሮ ወደሁለቱ ሀገሮች ለመጓዝ ቪዛ እንደማያስፈልጋቸው አስታውቀዋል፡፡

በሌላ ዜና የኤርትራ መንግሥት በቅርብ ወራት ጥብቅ ከሆነው የብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት ምልመላ ዘመቻው ጋር በተያያዘ ከምልመላ ያመለጡ ተብለው የተወነጀሉ በሺዎች የተቆጠሩ ሰዎች ቤተሰቦችን እየቀጣ ነው ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች ተናገረ፡፡

የኤርትራ ኃይሎች የኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ “የኢትዮጵያ መንግሥትን በመደገፍ በስፋት ተሳትፈዋል፡፡ እጅግ አስከፊ የመብት ጥሰቶችም ፈጽመዋል” ሲል ሂዩማን ራይትስ ዋች ወንጅሏል፡፡

የኤርትራ ባለሥልጣናት ከብሄራዊ ውትድርና ያመለጡ ወይም ከአገልግሎት የሸሹ ያሏቸውን ለመያዝ በስፋት አፈሳ አካሂደዋል” ብሏል፡፡

XS
SM
MD
LG