በኦሮምያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን ደምቢ ዶሎ ከተማ ውስጥ ትናንት፣ ሃሙስ ከማለዳ ጀምሮ ቀበሌ 03 አካባቢና ከተማዪቱ መግቢያ 05 ቀበሌ አካባቢ ከፍተኛ ተኩስ መስማታቸውን ነዋሪዎች ለቪኦኤ ዘጋቢ በስልክ ተናግረዋል።
ተኩሱ የተካሄደው በመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎችና ባለሥልጣናቱ “ሸኔ” በሚሉት የኦሮሞ ነፃነት ጦር እንደሆነ በሚናገረው ቡድን ታጣቂዎች መካከል ነው ብለው እንደሚጠረጥሩ ነዋሪዎቹ አክለው ገልፀዋል።
ተኩሱ ከበረደ በኋላ የመንግሥት ታጣቂዎች በመኪና ሆነው “ከእሥር ቤት የወጣችሁ ተመልሳችሁ ግቡ” እያሉ በድምፅ ማጉያ ሲያስነግሩ መስማታቸውን አንድ ነዋሪ አመልክተዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ቨርጂኒያ የሚገኙት የቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ታጣቂዎቻቸው ደንቢ ዶሎ ከተማ ውስጥ ጥቃት ማድረሳቸውን፣ የመንግሥት ታጣቂዎችን መግደላቸውንና መማረካቸውን፣ እንዲሁም እሥረኛ ማስመለጣቸውን ለቪኦኤ ተናግረዋል።
ተፈፀመ ስለተባለው ጥቃት ከአካባቢውም ሆነ ከክልሉ ባለሥልጣናት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ቪኦኤ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።