የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን፣ አንድ ትልቅ የቻይና ፊኛ የአሜሪካን የአየር ክልል ጥሶ በመገኘቱ በበጄኒንግ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት ማስተላለፋቸውን አስታወቁ፡፡
ብሊንክን በመጭዎቹ ቀናት ወደ ቤጂንግ በመጓዝ ከቻይናው መሪ ሺ ጄንፒንግ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር እንደሚነጋገሩ ተጠብቆ ነበር፡፡
የታቀደው ጉዞ ተመልሶ መች እንደሚደረግ ባለሥልጣናቱ አላብራሩም፡፡
ቻይና ሰሞኑን በዩናይትድ ስቴትስ አላስካ ክፍለ ግዛት እና ሞንታና ከተማ ውስጥ የአሜሪካ ባለሥልጣናት ሲከተላሉት የቆዩት ትልቅ ፊኛ የሷ መሆኑን አምናለች፡፡
ከመስመሩ የወጣ የአየር ሁኔታን የመቆጣጠሪያ ፊኛ መሆኑንም ቻይና ዛሬ በሰጠችው መግለጫ አስታውቃለች፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ከንግድ የአየር ትራንስፖርት በረራዎች በላይ ከፍ ብሎ ሲበር የተገኘውን ፊኛ ምንነት እየመረመሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
የተባለው ፊኛ በምድር ባሉ ሰዎችም ሆነ በንብረቶች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት የማያደርስ መሆኑንም ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል፡፡