በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የደቡብ አፍሪካው ኃይል መቆራረጥ ጤና ላይ ችግር እየፈጠረ ነው


ፎቶ ፋይል፦ ሶዌቶ፤ ደቡብ አፍሪካ 09/28/2022
ፎቶ ፋይል፦ ሶዌቶ፤ ደቡብ አፍሪካ 09/28/2022

በደቡብ አፍሪካ እየተባባሰ የመጣውን የመብራት ኃይል መቆራረጥ ለመቆጣጠር መንግሥት “የኃይል ሸክም ማቅለያ” (loadshedding) ስልቶችን ቢጠቀምም ለጤንነት አደጋ የተጋለጡ ሰዎችም ላይ ሆነ በአስቸኳይ ህክምና አገልግሎቶች ላይ መጨናነቅ መፍጠሩ ተነገረ።

በኃይል መቆራረጥ ሳቢያ የተፈጠረው ችግር የህክምና ሥራዎችን ለማከናወን አዳጋች ያደረገ ሲሆን ለሆስፒታሎች የተመደቡ ጀኔተሮችም መስራት ማቆማቸውን የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በቀዶ ጥገና ክልፍ የሚሰሩ ሀኪሞች፣ በማገገሚያ ክፍል ያሉ ህሙማንን ሙቀትና ቅዝቃዜ ለመጠበቅ፣ በሰዓታት በእጃቸው ለማራገብ መገደዳቸውንም፣ የህክምና ባለሙያዎቹ ስካይ ለተባለው የእንግሊዝ ዜና ማሰራጫ ተናግረዋል።

ህሙማንን ወደ ሆስፒታል ፈጥነው የሚያመጡ የአስቸኳይና አደጋ ጊዜ ተሽከካሪዎችም፣ የመንገድ ትራፊክ መብራቶች የማይሰሩ በመሆናቸው፣ ተሽከርካሪዎች ውስጥ ባሉ ለአጭር ጊዜ በሚሰሩ ጀኔረተሮች እየታገዙ ህሙማንን ለማጓጓዝ መገደዳቸውን ገልጸዋል።

ደቡብ አፍሪካ ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚችሉ እንደ ነፋስና ሶላር የመሳሰሉትን እንደ አስቸኳይ የታዳሽ ኃይል ምንጮች ለመጠቀም ብታስብም ያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ሆኖ መፍትሄ ይሰጣል የሚል እምነት አለማሳደሩ ተመልክቷል።

XS
SM
MD
LG