በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሶማሊያ አጎራባቾች አልሸባብ ላይ አዲስ ዘመቻ ሊከፍቱ ነው


የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጉሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሳን ሼህ እና የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጉሌ፣ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሳን ሼህ እና የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ

የጅቡቲ፣ የኢትዮጵያ እና የኬንያ መሪዎች የአልሸባብ ተዋጊዎችን ከአጎራባቿ ሶማሊያ ለማስወጣት በአዲሱ “የማሰስ እና መደምሰስ” ዘመቻ ለመሳተፍ መስማማታቸውን ዛሬ ረቡዕ አስታውቀዋል፡፡

የመሪዎቹ ውሳኔ የመጣው የሶማሊያ ፌዴራል መንግሥት በአልቃይዳ በሚደገፈው የአልሸባብ ቡድን ላይ ባለፉት ጥቂት ወራት ያደረገውን የተጠናከረ ጥቃት ተከትሎ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

የሶማሊያ መንግሥት በዩናትይድ ስቴትስ ጦር ከሚደገፉ የሶማሊያ የጎሳ ሚሊሻና ኃይሎች ጋር በመተባበር፣ በፌዴራሉ መንግሥት ቁጥጥር ስር የነበሩ፣ በማዕከላዊ ሶማልያ በርካታ ከተሞችና መንደሮችን ማስመለሱን የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

የኬንያ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ፣ የጅቡቲ ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጉሌ እና የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከሶማሊያው አቻቸው ፕሬዚዳንት ሀሳን ሼህ መሃሙድ ጋር በመሆን አልሸባብን ለማድከም የሚወሰዱ እምርጃዎችን ለመገምገም በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃድሾ መሰብሰባቸው ተመልክቷል፡፡

የመሪዎቹ “ስብሰባው በጋራ የታቀዱና የተደራጁ ጠንካራ ዘመቻዎችን በአገር አቀፍ ደረጃና በግንባር በሚገኙ ግዛቶች በማድረግ፣ በደቡብ እና ማዕከላዊ ሶማሊያ ቁልፍ የሆኑ በርካታ የአልሸባብ ይዞታዎችን አስሶ ለመደምሰስ መስማማቱን” በወጣው የጋራ መግለጫ ተጠቅሷል፡፡

“ከጊዜ አንጻር ጥንቃቄ የሚሻው ዘመቻ ወደፊት በአካባቢው ሊገጥሙ የሚችሉ ሰርጎ ገብነቶችን እንደሚያስቀር” ያመለከተው መግለጫው የዘመቻውን ዝርዝር ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡

ሦስቱ አገሮች በሶማሊያ ለአፍሪካን የሽግግር ተልእኮ በአፍሪካ ህብረት ለተጠየቀው የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ያዋጡ መሆኑም ተነግሯል፡፡

ዛሬ ረቡዕ ማለዳው ላይ ስብሰባው በተካሄደበት የፕሬዚዳንት ሼኽ መሃሙድ ጽ/ቤት አቅራቢያ የመለስተኛ ከባድ መሳሪያ (ሞርተር) ተኩስ ድምጽ ቢሰማም የደረሰ አደጋም ሆነ ጉዳት ስለመኖሩ የተነገረ ነገር የለም፡፡

ኬንያ ወታደሮችዋን ከሶማሊያ እንድታስወጣ ግፊት ለማድረግ አልሸባብ ኬንያ ውስጥ ጥቃቶችን ማካሄዱም በሮይተርስ ዘገባ ተመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG