አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ኩባንያ እንዲከሰስ የዩናይትድ ስቴትስ ፌደራል ፍርድ ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፣ በሁለቱ የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ላይ በደረሰው አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ዘመዶች በመጪው ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንደሚሰጡ ከፍርድ ቤታ ያገኘውን መረጃ ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
በቦይንግ 737 ሁለት አውሮፕላኖች ላይ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ እ.አ.አ በ2021 ዓ.ም የተደረሰውን ስምምነት፣ የተጎጂ ቤተሰቦች በመቃወማቸው የዩናይትድ ስቴትስ የወረዳ ፍርድቤት ዳኛ ሪድ ኦኮነር ፣ቦይንግ ኩባንያ ፍርድ ቤት ቀርቦ በወንጀል እንዲጠየቅ ውሳኔ ያሳለፉት ባለፈው ሳምንት ነበር።
ቦይንግ በ737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ላይ ከተገኘ የአሠራር ጉድለት ጋር በተያያዘ በቀረበበት የማጭበርበር ሴራ ክስ ዙሪያ፣ እ.አ.አ በጥር 2021 ዓ.ም የፍትህ ሚኒስቴር እንዲዘገይ ያደረገው የ2.5 ቢሊየን ዶላር የክስ ስምምነት ተፈራርሟል። በስምምነቱ መሰረትም ቦይንግ በወንጀል ያለመከሰስ ከለላ ማግኘት ችሎ ነበር።
በዚህ ዙሪያ ሀሳቡን እንዲሰጥ ሰኞ እለት የተጠየቀው ቦይንግ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል። የተጎጂ ቤተሰቦች የፍትህ መስሪያቤቱ "ዋሽቷል፣ በሚስጥር ባካሄደው ሂደትም መብታችንን ጥሷል" ሲሉ በመከራከር ዳኛ ኦኮነር የቦይንግን በወንጀል ያለመከሰስ መብት እንዲያነሱ ጠይቀዋል።።
ዳኛ ኦኮነር በጥቅምት ወር ባሳለፉት ውሳኔ በሁለቱ በተከሰከሱት የቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኖች ህይወታቸውን ያጡ ሰዎች በህግ ፊት "የወንጀል ሰለባዎች" ተደርገው ይወሰዳሉ ብለዋል። የቤተሰብ አባላትም ቦይንግ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ መሰረት ክስ እንዲቀርብበት አሳስበዋል።
እ.አ.አ በ2018 እና በ2019 በኢንዶኔዥያ እና በኢትዮጵያ የደረሱት የመከስከስ አደጋዎች ቦይንግ ከ20 ቢሊየን ዶላር በላይ እንዲያወጣ ያደረጉት ሲሆን ከፍተኛ ሽያጭ የነበረው አውሮፕላን ለ20 ወራት ከበረራ እንዲታገድ ሆኗል። የዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤትም የአውሮፕላን ጥራት ማረጋገጫን የሚያሻሽል ህግ እንዲያፀድቅ አድርገዋል።
በክስ ሂደቱ ላይ ቃላቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ከሚጠበቁት መካከል በአደጋው ሶስት ልጆቹን፣ ሚስቱን እና አማቱን ያጣው ፖል ኞሮጌ እና ሴት ልጃቸውን ሳሚያ ሮዝ ስቱሞን ያጡት ናዲያ ሚለር እና ሚካኤል ስቱሞ እንደሚገኙበት የፍርድ ቤቱ መዝገብ ያሳያል።
በአውሮፕላን አደጋዎቹ ህይወታቸው ካለፈው 346 ሰዎች መካከል የጥቂቶቹን ዘመዶች የወከሉት ጠበቃ ፖል ካሴል እንደሚሉት "ቤተሰቦቹ በችሎቱ ላይ ለሚወዷቸው ሰዎች ሞት ተጠያቂ ስለሆነው ኩባንያ ለመናገር በጉጉት እየተጠባበቁ ነው።"
ቦይንግም ሆነ የፍትህ ሚኒስቴር፣ ለተጎጂ ቤተሰቦች ካሳ የሚውል የ500 ሚሊየን ዶላር ፈንድ፣ 243 ሚሊየን ዶላር የቅጣት ክፍያን እና ለአየር መንገዶች የሚከፈል የ1.7 ቢሊየን ዶላር ካሳ የሚያጠቃልለውን የክስ ስምምነት ጥሶ ክሱ እንደገና መከፈቱን ይቃወማሉ።
ቦይንግ በህዳር ወር ስምምነቱን እንደገና ለመክፈት የሚደረገን ማንኛውም ጥረት እንደሚቃወም ተናግሮ፣ ይህ "ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ፣ የማይሰራ እና ፍትሃዊ ያልሆነ" ነው ሲል ገልጿል። ስምምነቱን ለሁለት ዓመታት ያህል ሲያከብር መቆየቱንም አመልክቷል።