በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የፈረንሳይ ወታደሮች ቡርኪና ፋሶን ለቀው እንዲወጡ የአንድ ወር ዕድሜ ተሰጣቸው


ፎቶ ፋይል - የቡርኪና ፋሶ ተቃዋሚዎች የፈረንሳይ ጦር ከአገራችን እንዲወጣ የሚጠይቅ መፈክር ይዘው፤ በዋጋዱጉ፣ ቡርኪናፋሶ
ፎቶ ፋይል - የቡርኪና ፋሶ ተቃዋሚዎች የፈረንሳይ ጦር ከአገራችን እንዲወጣ የሚጠይቅ መፈክር ይዘው፤ በዋጋዱጉ፣ ቡርኪናፋሶ

“ቡርኪና ፋሶ በግዛቷ የሚንቀሳቀሱትን ሸማቂዎች ለመዋጋት ለፈረንሳይ ወታደሮች የሚፈቅደውን ወታደራዊ ስምምነት ለማብቃት ወስናለች” ሲል የሃገሪቱ መንግስት ትላንት አስታወቀ።

ከአልቃይዳ እና ከጽንፈኛው ኢስላማዊ ቡድን ጋር ቁርኝት ያላቸውን ቡድኖች ዳግም እያንሰራራ የመጣ ጥቃት በመጋፈጥ ላይ ያለችው ምዕራብ አፍሪካዊቱ ሃገር በጥቃቶቹ መጠነ ሰፊ መሬቷ ተወስዶ እና በሚሊዮን የሚቆጠረው ሕዝቧም በሰፊው የሳህል ክልል ተፈናቅሎ ይገኛል።

ባለፈው ቅዳሜ ጥር 13, 2015 የሃገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን መንግሥት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ጥር 18/2018 ከፓሪስ ጋር ያደረገውን ወታደራዊ ሥምምነት ማቋረጡን እና ፈረንሳይ ወታደሮቿን እንድታወጣ የአንድ ወር ጊዜ መስጠቱን ይፋ አደረገ።

በማግስቱም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከሽግግሩ ፕሬዚዳንት ኢብራሂም ትራኦሬ ማብራሪያ እየጠበቁ መሆናቸውን ተናገሩ።

ይሁንና ትናንት ሰኞ የመንግሥት ቃል አቀባይ ሪምታልባ ዣን ኢማኑኤል ኦውድራጎ በሰጡት አስተያየት "ከዚህ የበለጠ እንዴት ግልጽ መሆን እንደምንችል አናውቅም" ሲሉ መልሰዋል።

እንደ ኦውድራጎ ገለጻም የቡርኪናቤ የሽግግር መንግስት ራዕይ ሃገራቸው እራሷን መከላከል እንድትችል ነው። ከፈረንሳይ ጋር የነበራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያለማብቃቱን እና ቡርኪናፋሶ አሁንም በወታደራዊ መሳሪያዎች መልክ ድጋፍ እንደምትፈልግም አክለው ተናግረዋል። የፈረንሳይ ባለሥልጣናት አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም።

በሌላ በኩል ፈረንሳይ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ በነበሩ አገሮች ውስጥ የነበራት ተጽእኖ እየቀነሰ መምጣቱ ተስተውሏል።

ባለፈው አርብ ጥር 12, 2015 ዓም ኡጋዱጉ ላይ የተሰባሰቡ በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎች የፈረንሳይን ጦር “ውጡ” የሚል ጥሪ ሲያሰሙ እና የፈረንሳይን ባንዲራ ሲያቃጥሉ ታይተዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ሥልጣን በተቆጣጠሩ ወታደራዊ ጁንታዎች የሚተዳደሩት ቡርኪና ፋሶ እና ጎረቤት ማሊ ከቀድሞ አጋሮቻቸው ጋር የነበሯቸውን ግንኙነቶች አፍርሰዋል።

በተመሳሳይም የግንኙነታቸውን መበላሸት ተከትሎ የፈረንሳይ ወታደሮች ባለፈው ዓመት ማሊን ለቀው መውጣታቸው ይታወሳል።

የፈረንሳይ ጦር ማሊን ለቆ የወጣበትም ሰዓት ማሊን የሚያስተዳድረው ኃይል እየጠነከረ የመጣውን የሸማቂዎች ጥቃት ለመዋጋት እንዲረዳው የሩስያ ቅጥረኛ ወታደሮችን ለመቅጠር ከወሰደው እርምጃ ጋር ተገጣጥሟል።

ማክሮን ሩሲያ “ችግር ውስጥ የገቡ” ባሏቸው የአፍሪካ አገሮች ውስጥ "አድብታ በምታደርገው እንቅስቃሴ" ተጽእኖ እያደረገች ነው ሲሉ ወንጅለዋል።

በተያያዘም ቡርኪና ፋሶ የሩሲያውን ወታደራዊ ቡድን ዋግነርን ለመቅጠር ወስናለች የሚለውን በቅርቡ የወጣ ዘገባ አላመነችም ወይም አላስተባበለችም።

XS
SM
MD
LG