በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከቅዱስ ሲኖዶስ እውቅና ውጭ የጳጳሳት ሹመት ተፈጽሟል ስትል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አስታወቀች


ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ ፓትረያርክ፣ ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ወሊቀ-ጳጳስ ዘአኵስም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ-ተክለኃይማኖት
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፤ ፓትረያርክ፣ ርዕሰ-ሊቃነ-ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ወሊቀ-ጳጳስ ዘአኵስም፣ ወእጨጌ ዘመንበረ-ተክለኃይማኖት

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዛሬ በሰጠችው መግለጫ ቅዱሱ ሲኖዶሱ የማያውቀው የጳጳሳት ሹመት መከናወኑን አስታውቃለች።

መግለጫውን የሠጡት የቤተክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃምና በመንበረ ፓትርያርክ የተገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ስለመሆናቸው ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንበረ ፓትሪያርክ ጠቅላይ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በቤተ ክርስቲያኒቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈው መግለጫቸው ላይ ስለተፈጸመው ድርጊት የገለጹት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጭ ያሉ ሊቃነ ጳጳሳትን ለአስቸኳይ ስብሰባም ጠርተዋል፡፡

ቤተክርስቲያኒቷ ሕገ-ወጥ ስትል ያወገዘችው የጳጳሳት ሹመት የትና በማን እንደተከናወነ ግን ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስም ሆኑ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም በሰጡት መግለጫ ላይ አልተመለከተም፡፡

ይሁን እንጂ በተለያዩ ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን እየተዘዋወሩ ባሉ መረጃዎች፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በወሊሶ በዓለ ወልድ ቤተ ክርስቲያን "ጳጳሳትን" መሾማቸው እየተገለጸ ነው፡፡ ሆኖም የአሜሪካ ድምጽ፣ ዛሬ ተፈጽሟል ስለተባለው የጳጳሳት ሹመት ጉዳይ እስካሁን ከሚመለከታቸው አካላት ማጣራት አልቻለም፡፡ በድርጊቱ ላይ ተሳትፈዋል ከተባሉ አካላት በኩልም፣ ስለሹመቱ እስካሁን በግልጽ የተባለ ነገር የለም፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስም ሆኑ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ዛሬ በሰጡት መግለጫ፣ በጉዳዩ ላይ በመወያየት ውሳኔ ለማሳለፍ አስቸኳይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ ከመጥራት በተጨማሪ፣ መንግሥት ክስተቱ በሀገር ላይ ጭምር የሚያስከትለውን ጉዳት ተመልክቶ ሕጋዊ ሓላፊነቱን እንዲወጣ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ከመንግስት በኩል ግን እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ይፋዊ አስተያየት አልተሰጠም፡፡

XS
SM
MD
LG