በአልሸባብ ተዋጊዎች የተቀበረ መሆኑ የተገለፀ የጦር መሳሪያ መደበቂያ ስፍራ በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ መያዙን የሶማሊያ ባለስልጣናት ትላንት አስታወቁ።
በምህፃረ ቃሉ 'ኒሳ' በመባል የሚጠራው የሀገሪቱ ብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ኤጀንሲ ባወጣው መግለጫ በአልሻባብ ታጣቂዎች ተቀብረዋል የተባሉት መሳሪያዎች የተገኙት የሶማሊያ የስለላ ድርጅት እና የሞቃዲሾ ክልል ፖሊስ ጥምር ቡድን ባካሄዱት የጋራ እንቅስቃሴ ነው።
መግለጫው አክሎ የፀጥታ ሀይሎች የአልሸባብ አባል መሆኑ የተጠረጠረ ግለሰብ ፖሊስ ብረበራ ባካሄደበት ዳርከንሌይ ወረዳ የሚገኝ መኖሪያ ቤት ውስጥ መያዙን ጠቅሷል።
አንድ ስማቸው እንዳይገለፅ የጠየቁ የኒሳ ባለስልጣን ለአሜሪካ ድምፅ እንደገለፁት ከተያዙት የጦር መሳሪያዎች ውስጥ የተሻሻሉ ሽጉጦች፣ ቦምቦች፣ ጥይቶች እና ሌሎች ፈንጂዎች ይገኙበታል።
ትላንት ምሽት የፀጥታ ኃይሎች ሞቃዲሾ በሚገኝ ቤት ላይ ያካሄዱት ብርበራ፣ መንግስት አልሻባብን ለማሸነፍ እና በሶማሊያ የሚያደርሱትን የሽብር ጥቃቶች ለመከላከ እያካሄደ ያለው ዘመቻ አካል መሆኑ ተገልጿል።