በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሰዎችን በማዘዋወር የተጠረጠረው ኤርትራዊ ኔዘርላንድ ፍ/ቤት ቀረበ


በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር መረብ ውስጥ ተሳትፎ አለው በሚል የተጠረጠረው ኤርትራዊ ተወልደ ጎይቶም ዛሬ የቅድመ ፍርድ ሂደቱን ለመስማት በኔዝርላንድ በሚገኝ ፍ/ቤት ቀርቧል።

አቃቤ-ሕግ በተጨማሪም የሕገ-ወጥ ሰዎች አዘዋዋሪ ቡድን መሪ የተባለውንና በቅርቡ በሱዳን የተያዘውን ሌላ ኤርትራዊ ኪዳኔ ዘካሪያስ ሃብተማሪያም ለኔዘርላንድ ተላልፎ እንዲሰጥ ጠይቋል።

ተወልደ ጎይቶም ዛሬ በነበረው የፍ/ቤት ቆይታ በአስተርጓሚው በኩል ለዳኞች እንደተናገረው ከሳሾቹ በመልክ መመሳሰል ምክንያት እሱን ወንጀለኛ በማድረጋቸው ለዚህ መብቃቱን ተናግሯል።

ከሳሽ አቃቤ-ሕግ በበኩሉ ትክክለኛው ሰው መያዙን የመሰከሩ ሰዎች አሉኝ ብሏል። የአገሪቱ ብሔራዊ ምርመራ ቢሮ የተወልደ ጎይቶምን ማንነት ለማጣራት ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።

ተወልደ ጎይቶም ባለፈው ዓመት ከኢትዮጵያ ወደ ኔዝርላንድ ተላልፎ መሰጠቱን የአሶስዬትድ ፕረስ ሪፖርት አስታውሷል።

የተበዳይ ቤተሰቦች በኔዘርላንድ ስለሚኖሩ ተወልደ ጎይቶምን በኔዘርላንድ ለመክሰስ በቂ ምክንያትና ሥልጣን እንዳላቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።

ተከሳሾቹ በሊቢያ በሚቆጣጠሩት ካምፕ ውስጥ ፍልሰተኞች ላይ ድብደባ፣ ስቃይና አስገድዶ መድፈር ፈጽመዋል ሲል የኔዘርላንድ አቃቤ-ሕግ ይከሳል።

በኔዘርላንድ የሚኖሩ ቤተሰቦች ፍልሰተኞቹን ለማስለቀቅ ገንዘብ እንዲከፍሉ ተገደዋል፣ ተከሳሾቹም ፍልሰተኞቹን በጀልባ ወደ አውሮፓ ላማሻገር ሲሞክሩ በርካቶች ባህር ላይ ሞተዋል ሲል አቃቤ-ሕግ በተጨማሪ ይከሳል።

የተከሳሾቹ ጠበቃ የኔዘርላንዱ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን አለው የሚለውን እንደሚሞግቱ አስታውቀዋል።

ፍርድ ቤቱ ለመጋቢት 27 ቀን 2015 ዓ/ም ተቀጥሯል።

XS
SM
MD
LG