በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ካለምንም አድልዎ ሁሉንም እያስተናገደ መሆኑን ገለጸ


ፎቶ ፋይል፦ ጉያ የተፈናቃዮች መጠለያ፤ ከአፋር ክልል ሰመራ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ፣ እአአ 9/2022
ፎቶ ፋይል፦ ጉያ የተፈናቃዮች መጠለያ፤ ከአፋር ክልል ሰመራ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ፣ እአአ 9/2022

ዓለም አቀፉ ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን፣ ሜዲሳን ሳን ፍራንቴር (ኤምኤስኤፍ) በኢትዮጵያ የጤና አገልግሎት እጅግም በማይዳረስባቸው አካባቢዎች አስቸኳይ የህክምና እና ሰብዓዊ ዕርዳታ እያደረገ መሆኑን ለቪኦኤ በላከው የጽሁፍ መግለጫ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሰብዓዊ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ያወሳው ድርጅቱ በግጭት ምክንያት በተለይም በአፋር፣ አማራ፣ ትግራይ እና ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ ያሉ ማኅበረሰቦች ዕርዳታ እንደሚሻቸው ገልጿል።

በሶማሌ ክልል በሲቲ ዞን፣ ተንቀሳቃሽ የማረጋጊያ ክሊኒኮች በማቆም ወደ 2,600 የሚጠጉ ሰዎች የህክምና ድጋፍ እንደሰጠ ድርጅቱ አስታውቋል።

በዚሁ ክልል፣ ሊባን ዞን 75,000 የሚጠጉ የተፈናቀሉ ሰዎች የሚኖሩበት አዴሌ ካምፕ በኮሌራ ወረርሽኝ ክፉኛ የተጠቃ በመሆኑ ቡድኑ የኮሌራ ህክምና ማዕከላትን ማቋቋሙን እንዲሁም ተፈናቃዮቹ ንጹህ የመጠጥ ውሀ እንዲያገኙ የውሀ ማጣሪያዎችን፣ የእጅ መታጠቢያ ገንዳዎች፣ 12 መጸዳጃ ቤቶችን መገንባቱን አስታውቋል።

በአማራ ክልል በግጭት የተጎዱ በርካታ ማኅበረሰቦች መኖራቸውንና አብዛኛዎቹ ታካሚዎች በድብርት የተጠቁ ናቸው ያለው ድርጅቱ ከጾታዊ ጥቃት ጋር የተያያዙ ብዙ መገለሎች እንዳሉም ጠቁሟል።

ከ50,000 በላይ የሚሆኑ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ተጠልለው በሚኖሩበት በኩሌ ካምፕ የኤምኤስኤፍ የህክምና ቡድን የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ የጤና አጠባበቅ አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ እንዲሁም ተመላላሽ ታካሚዎችን እንደሚቀበል በመግለጫው ተመልክቷል።

XS
SM
MD
LG