በኬንያ የታዳጊዎች እርግዝና ችግር ለመቅረፍ በዲጂታል አገልግሎት የሚሰጥ የወሲብ ትምህርት መጀመሩ ከ5ሺህ በላይ ወጣቶችን መሳብ እንደቻለ የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ። በስዋሂሊ ቋንቋ 'ኔና ና ቢንቲ' ወይም 'ከአንድ እህት ጋር ተነጋገሩ' የተሰኘው አገልግሎት በሞባይል መተግበሪያ እና ከክፍያ ነፃ በሆነ የስልክ ጥሪ አማካኝነት፣ በእርግዝና መጠን በዓለም ሦስተኛ ከፍተኛ ደረጃ ለያዙት የኬንያ ታዳጊዎች፣ በስነ-ተዋልዶ ጤና ዙሪያ መረጃ እና የምክር አገልግሎት ይሰጣል።
ኬንያ በቅርቡ ይፋ ያደረገችው ብሄራዊ መረጃ እንደሚያሳየው ከአምስት ታዳጊ ልጃገረዶች መካከል አንዷ በ19 አመቷ እናት ትሆናለች። በአሥራዎች ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ ታዳጊዎች እርግዝና ኬንያ በዓለም በሦስተኛ ድረጃ ላይ ትገኛለች። በመሆኑም የእርዳታ ቡድኖች የወሲብ ትምህርት በዲጂታል መንገዶች በማቅረብ ችግሩን ለመቅረፍ እየሞከሩ ነው።
በስዋሂሊ ቋንቋ 'ኔና ና ቢንቲ' ወይም ወደ አማርኛ ሲመለስ 'ከአንድ እህት ጋር ተነጋገሩ' የተሰኘው የሞባይል መተግበሪያ ለታዳጊዎች ስለ ስነ-ተዋልዶ ጤና መረጃ እና ከአማካሪ ባለሙያዎች ጋር በርቀት የመነጋገር እድል ይሰጣል። ለመተግበሪያው ተጠቃሚዎችም የስልክ ቁጥሮችን ይሰጣል።
ጃኔት አዊኖ መድረኩን በተለይ ለቤተሰብ ምጣኔ ትምህርት እየተጠቀሙ ካሉ ቢያንስ 5ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች መካከል አንዷ ናት።
"በአካል ከማላየው ሰው ጋር ነው የምነጋገረው፣ ያ ደግሞ በግልፅ እንዳወራ ይረዳኛል። ከማንም ሰው ጋር ስለዚህ ማውራት አልችልም፣ ምክንያቱም አንዳንድ ሰዎች ሚስጥር መጠበቅ አይችሉም።"
የአንድ ልጅ እናት የሆነችው ቨርጂኒያ ሙቺራ መተግበሪያ እየሰጠው ያለው የስነ-ተዋልዶ ጤና መረጃ ለሷም ይጠቅማት እንደነበር ትገልፃለች።
"እናቴ እና አባቴ ስለዚህ ጉዳይ ሊያስተምሩኝ የሚችሉ ሰዎች አልነበሩም። የምንገናኘው ለምግብ ጠረጴዛ ላይ ስንቀመጥ ነው። ከዛ ሁሉም ወደየአቅጣጫው ይሄዳል። ስለሌላ ነገር ሊያወሩ ይችላሉ፣ ስለ ስነ-ተዋልዶ ጤና ግን አያወሩም። ስለዛ ጉዳይ አይነግሩኝም።"
የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስትር በመስከረም ወር ያካሄደው ጥናት እንደሚያሳየው በሥነ-ተዋልዶ ጤና ላይ ያለው የመረጃ እጥረት በአስራዎቹ እድሜ ውስጥ ያሉ እርግዝናዎች እንዲባባሱ አስተዋጽኦ አድርጓል። ባለሙያዎች እንደሚሉትም፣ አብዛኞቹ ታዳጊዎች ስለወሲብ እና የስነተዋልዶ ጤና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማውራት ይፈራሉ። ሪታ ኦቦኞ የስነ ተዋልዶ ጤና መረብ ውስጥ የሚያገለግሉ ሲሆን ይህን አይነት መረጃ ማግኘት ግን ችግሩን ለረጅም ግዜ ለማስተካከል ሊረዳ ይችላል ይላሉ።
"አብዛኞቹ የሚደውሉት ደንበኞች እድሜያቸው ከ10 እስከ 17 የሆኑ ታዳጊዎች ከሆኑ ማወቅ የሚፈልጉት ስለየወር አበባ ነው። ሌሎች ለእርግዝና የማይጋለጡበት ግዜ የትኛው እንደሆነ ለማወቅ ይፈልጋሉ። አንዳንዶች ደግሞ የወሊድ መቆጣጤሪያ ሊኖረው ስለሚችለው ተፅእኖ ለማወቅ ፈልገው ይደውላሉ። "
የክልሉ ባለስልጣናት ወጣት እናቶችን በሚጠቅሙ ፕሮግራሞች ውስጥ እንዲረዱ በማህበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶችን እያሰለጠኑ መሆናቸውን ይገልፃሉ። ክርስቲን ኦዱል ከነዚህ የማህበረሰብ ጤና በጎ ፈቃደኛ አገልጋዮች አንዷ ናት።
"አንዳንዶቹ ወደ ትምህርት ቤት መመለስ ስለሚፈልጉ ወደ ትምህርት ቤት እንወስዳቸዋለን። ሌሎቹ ትምህርት መቀጠል እንደማይችሉ ስለሚናገሩ የሙያ ስልጠና እንሰጣቸዋለን። አንዳንዶቹም ተቀጥሮ ስለመስራት እና የራስን ንግድ ስለመጀመር ይማራሉ።"
የኬንያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በጉርምስና እና ወጣትነት እድሜ የሚገኙ ልጆች ሊያጋጥሟቸው የሚችሉትን የስነ ተዋልዶ ጤና ችግሮችን ለመቅረፍ እና ሌሎች ጉዳዮችንም ያካተተ የ10-አመት ብሄራዊ የስነ-ተዋልዶ ጤና ፖሊሲ ሐምሌ ወር ላይ አጽድቋል። ልክ እንደ 'ኔና ና ቢንቲ' ያሉ እንቅስቃሴዎችም በመጪዎቹ አመታት የታዳጊዎችን እርግዝና ለመቆጣጠር የሚደረገውን ጥረት ያበረታታል ብለው ባለስልጣናት ተስፋ ያደርጋሉ።