በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሊቢያ 700 የሚደርሱ ስደተኞችን ጭና ወደ አውሮፓ ስትጓዝ የነበረች መርከብ ያዘች


ሊቢያ፣ ግበጽ እና የሜዲትራኒያን አካባቢ
ሊቢያ፣ ግበጽ እና የሜዲትራኒያን አካባቢ

ከ700 ያላነሱ ሰደተኞችን አሳፍራ የነበረች መርከብ በሊቢያ ምሥራቃዊ የባህር ጠረፍ መያዟን የሊቢያ የባህር ጠረፍ ጠባቂ ገለጸ። በጦርነት በምትታመሰው ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር በኩል፤በአውሮፓ የተሻለ ኑሮ በመሻት ከሚጓዙ ስደተኞች፤ በቅርብ ወራት ከታዩት ሁሉ የአሁኑ ትልቁ ነው።

ጀልባዋ አርብ ዕለት ከምስራቃዊ ቤንጋዚ በ90 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ሞራ ከተባለች ከተማ አካባቢ እንደተያዘች የባህር ዳርቻ ጠባቂዎች አስታውቀዋል።

ሰደተኞቹ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በህገ ወጥ መንገድ ሊቢያ የገቡትም ወደ የመጡበት ሀገር ተላልፈው እንደሚሰጡ መግለጫው አስታውቋል። ይሁን እንጂ መግለጫው ተጨማሪ ዝርዝሮችን አላስቀመጠም።

ሊቢያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአውሮፓ የተሻለ ኑሮ ለሚፈልጉ ስደተኞች ዋና መሸጋገሪያ ሆናለች። በ2011 የረዥም ጊዜ ገዢ የነበሩትን ሞአማር ጋዳፊን ከስልጣን አስወግዶ የገደለውን በሰሜን አትላንቲክ የቃልኪዳን ጦር የተደገፈውን ህዝባዊ አመጽ ተከትሎ፤ በነዳጅ ዘይት የበለፀገችው ሀገር ቀውስ ውስጥ ገብታለች።

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት በሜዲትራኒያን ባህር 1,522 ሰዎች መሞታቸውን እና መጥፋታቸውን ዘግቧል። በአጠቃላይ እ.ኤ.አ ከ2014 አንስቶም 24,871 ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ሞተዋል ወይም ጠፍተዋል ሲል ተቋሙ አክሎ ገልጿል። ይሁን እንጂ ሪፖርት ያልተደረጉ የመርከብ መሰበር ጉዳቶችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት እውነተኛው አሃዝ ከዚህ ሊልቅ እንደሚችል ተጠቁሟል።

XS
SM
MD
LG