በጋና በ21 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበው የዋጋ ግሽበት የዘንድሮው የገና እና የዘመን መለወጫ በዓላት ለብዙዎቹ ሰዎች ከባድ እንዲሆን ማድረጉ ተነገረ፡፡
የኮቪድ 19 ወረረሽኝ እና የዩክሬን ጦርነት ግፊት ተጨምሮ በጋና የዋጋ ግሽበቱ 50.3 ከመቶ መድረሱ ተመልክቷል፡፡
በዚህ የተነሳም እጅግ የናረውን የዋጋ ውድነት መቋቋም ያቃታቸው ብዙዎቹ ጋናዊያን ወጭዎቻቸውን እንዲቆጥቡ መገደዳቸው ተነግሯል፡፡
ባህላዊ የሆነውን የበዓል ጊዜ ጉዞ ጨምሮ፣ ብዙዎቹ አገር ቤት ወዳሉት ቤተሰቦቻቸውና ዘመዶቻቸው በመሄድ የሚያሳልፉትን ጊዜ ለመሰረዝ እንደተገደዱም ተመልክቷል፡፡
የዓለም ባንክ በጋና ያለው የምግብ ዋጋ ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገሮች እጅግ ከፍተኛው መሆኑን ገልጿል፡፡
የምግብ ዋጋ ካለፈው ዓመት በእጥፍ መጨመሩን የገለጸው ባንኩ የዳቦ ዋጋ በሦስት እጥፍ ያህል ማደጉንም አስታውቋል፡፡
የጋና መንግሥት ባላፈው ህዳር የወጭ ቅነሳ ሲያውጅ፣ የአዲስ ሠራተኞችንም ቅጥር አቋርጧል፡፡ ኢኮኖሚውንም ወደ ሥፍራው ለመመለስም ተጨማሪ የእሴት ታክስ ጥሏል፡፡
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም የጋና ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የ3 ቢሊዮን ዶላር ብድር ድጋፍ ለማድረግ በዚህ ወር መስማማቱ ተመልክቷል፡፡