ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ተሳታፊ የነበሩት የኤርትራ ወታደሮች ከሽረ እና ከአክሱም ለቀው ወደ ድንበር አቅጣጫ በመሄድ ላይ ናቸው ሲሉ የዓይን ምስክሮች ለሮይተርስ ዜና ወኪል ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ መንግስት ፌዴራል ኃይሎችና በትግራይ ክልል ኃይሎች መካከል በነበረው ሁለት ዓመት የፈጀ ጦርነት፣ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያ ኃይሎችን በመደገፍ ተሳትፈዋል።
ኤርትራ ከዛሬ ሁለት ወር ገደማ በፊት የተፈረመው የሰላም ስምምነት አካል አይደለችም። ስምምነቱ ግን የውጪ ኃይሎች ከሰሜን ኢትዮጵያ እንዲወጡ ያዛል። ከስምምነቱ መፈረም በኋላ የኤርትራ ወታደሮች በትላልቅ የትግራይ ከተሞች መገኘት የስምምነቱ ዘላቂነት ላይ ጥያቄ አስነስቶ ነበር።
የኤርትራ ወታደሮች እስከወዲያኛው ትግራይን ለቀው ይውጡ ወይም ከተወሰኑ ከተሞች ብቻ ያፈግፍጉ መጀመሪያ ላይ ግልጽ አልነበረም። የኤርትራው ማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ከሮይተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወታደሮቹ ስለመውጣታቸው ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ አልሰጥም ብለዋል። አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የኢትዮጵያ መንግስት ባለሥልጣን ግን የኤርትራ ወታደሮች ከአክሱምና ሽረ እየለቀቁ መሆናቸውን ለሮይተርስ አረጋግጠዋል።
የትግራይ ኃይሎች ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳን እና የኢትዮጵያ መንግስት ብሔራዊ የጸጥታ አማካሪ ሬድዋን ሁሴን አስተያየታቸውን እንዲሰጡ ሮይተርስ ቢሞክርም ሊያገኛቸው አልቻለም።
በአክሱምና ሽረ ያሉ ሶስት የግብረ-ሰናይ ድርጅት ሠራተኞች እንዳሉት በርካታ የጭነት ተሽከርካሪዎችና ሌሎች መኪኖች ላይ የተጫኑ የኤርትራ ወታደሮች ድንበር ላይ ወዳለችው ሽራሮ ከተማ አቅጣጫ ሲሄዱ ማየታቸውን ተናግረዋል። ከዕርዳታ ሠራተኞቹ አንዱ አንዳንዶቹ ወታደሮችም የደህና ሁኑ ምልክት በእጃቸው ሲያሳዩ ነበር ብለዋል። አንድ የዕርዳታ ሠራተኛ ሁሉም የኤርትራ ወታደሮች ከሽረ ለቀዋል ሲሉ ሌላኛው ደግሞ በርካታ ቅጥር ያላቸው አሁንም በከተማዋ እንደቀሩ ተናግረዋል። የተለያየ ነገር መናገራቸው ምክንያቱ ግልጽ እንዳልሆነለት የሮይተርስ ዘጋቢ አመልክቷል።
ከሰላም ስምምነቱም በኋላ የኤርትራ ወታደሮች በሲቪሎች ላይ ዝርፊያ፣ እገታ እና ግድያ ፈጽመዋል ሲሉ በትግራይ ያሉ ነዋሪዎች ይወነጅሏቸዋል። የኤርትራ ባለስልጣናት ለውንጀላው ቀጥተኛ መልስ አይሰጡም።
የኤርትራ ወታደሮች በኅዳር 2013 በአክሱም በመቶ የሚቆጠሩ ሲቪሎችን በ24 ሰዓታት ውስጥ መግደልን ጨምሮ ሌሎች ሰቆቃዎችን ፈጽመዋል ሲሉ ነዋሪዎችና የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ይከሳሉ። ኤርትራ ውንጀላውን ታስተባብላለች።
ኤርትራ የትግራይ ሃይልን የሚመራው ህወሓትን እንደጠላት ማየቷን ቀጥላለች። ህወሓት የፌዴራል ስልጣኑን በበላይነት ይዞ በነበረበት ወቅት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል በ1990 ዎቹ መጀመሪያ ላይ ለሁለት ዓመታት የቆየ ጦርነት ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ መንግስትና የትግራይ ክልል ባለስልጣናት የሰላም ስምምነቱን ለመተግበር መጀመሪያ ፍጥነት ባያሳዩም፣ ባለፉት ሳምንታት ግን በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል።
ትናንት ሐሙስ የሁለቱ ወገን ተወካዮች በትግራይ መዲና መቀለ ተገናኝተው የትግራይ ኃይሎች መሳሪያ መፍታትን፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚቀጥልበትን እንዲሁም የውጪ ኃይሎች የሚወጡበትን ሁኔታ የሚቆጣጠር ቡድን አቋቁመዋል።
በሰላም ስምምነቱ መሠረት የፌዴራል ፖሊስ መቀሌ ሲገባ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ክልሉ የሚያደርገውን በረራ እንደገና ጀምሯል። ኢትዮ ቴሌኮምም መቀሌንና ሌሎች 27 ከተሞችን መልሶ አገናኝቷል።