በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ከተማ በፈረንጆች ገና ዋዜማ በደረሰው የነዳጅ ቦቴ ፍንዳታ የሞቱት ሠዎች ቁጥር 27 መድረሱን የከተማው ጤና ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
የቦቴው ፍንዳታ የታምቦ መታሰቢያ ሆስፒታል የድንገተኛ ክፍልን ጣሪያ ሲገነጥል፣ ሁለት ቤቶችን ሙሉ ለሙሉ አውድሟል፣ በርካታ ቤቶችን ደግሞ አፍርሷል። እስከ 1600 ጫማ ርቀት ላይ የነበሩ ሰዎችንም ጎድቷል።
የከተማው ጤና ባለሥልጣን እንዳስታውቀው ከሟቾቹ ውስጥ 10 የሚሆኑት የሆስፒታሉ ሰራተኞች ናቸው።
እንደ ሮይተርስ ዜና ወኪል ዘገባ ከሆነ፣ በመጀመሪያ 18 ሰዎች በፍንዳታው እንደሞቱ ባለሥልጣናት ቢያስታውቁም፣ ፍንዳታው በሰዎች ላይ በፈጠረው ከፍተኛ ቃጠሎ ምክንያት የሟቾቹ ቁጥር ጨምሯል።
የቦቴው ሹፌር በግድያ ተጠርጥሮ ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በቂ ማስረጃ አልተገኘበትም በሚል ትናንት ተለቋል ሲሉ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።