የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እስከ ሐሙስ ድረስ መቀሌ ከተማ እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ። በሰላም ስምምነቱ መሰረት ከባድ የጦር መሳሪያዎች ርክክብ እንደሚከናወንም ጠቁመዋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ወደ መቀሌ የመንገደኞች በረራ እንደሚጀምር ገልጿል።
የፌደራል መንግሥቱን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ያካተተ ልዑካን ቡድኑ ከመቀሌ ከተመለሰ በኋላ ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ማብራሪያ መሰጠቱን የጠቆሙት አምባሳደር ሬድዋን ፤ የተለያዩ አገልግሎቶችን ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ እየተሠራ ያለው ሥራ ይበልጥ እንዲፋጠን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መመሪያ መስጠታቸውን በጹሑፋቸው ላይ አስፍረዋል።
ይህን የጠቅላይ ሚኒስትሩን መመሪያ ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከነገ ረቡዕ ታህሣስ 19 ጀምሮ ወደ መቀሌ የመንገደኞች በረራ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ የመቀሌው አውሮፕላን ማረፊያ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል።
በቀን አንድ በረራ በማድረግ ወደ መቀሌ የሚያደርገውን ዕለታዊ በረራ እንደሚጀምር ለዝግጅት ክፍላችን በላከው የፁሁፍ መግለጫ ያረጋገጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በቀን የሚደረገው የበረራ መጠን እንደ መንገደኞች ፍላጎት ሊጨምር እንደሚችል ገልጿል።
የመቀሌ አውሮፕላን ማረፊያው ለአገልግሎቱ የሚያስፈልጉ ሁሉም ነገሮች ተሟልተውለት እንዳለ የገለጹት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን፣ “የቴሌኮሙኒኬሽን የኢንተርኔት አገልግሎትም ዛሬ ይጠናቀቃል” ሲሉ በመግለጫቸው አመልክተዋል፡፡
ኢትዮቴሌኮም በመቀሌ የኢንተርኔት አገልግሎቱን መቼ እንደሚጀምር በግልጽ ባያሳውቅም፣ እንደ አየር መንገድ ሁሉ “ኢትዮቴሌኮምም የአገልግሎቱን መጀመር ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል” ሲሉ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዛሬው ትዊታቸው አመልክተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እስከ ሐሙስ ድረስ መቀሌ ከተማ እንደሚገባም አምባሳደር ሬድዋን ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም “በሁለተኛው የናይሮቢ ውይይት ላይ በተደረሰው መግባባት መሠረትም እስከ ሐሙስ ድረስ ከባድ የጦር መሣሪያዎችን የመረካከብ እና የመከላከያ ሰራዊትም በተለይ በመቀሌ ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን መወጣት ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል” ብለዋል።
ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም የተፈረመው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት፣ የትግራይ ተዋጊዎችን ትጥቅ አፈታት በተመለከተ በአንቀጽ 6 ላይ፣ ስምምነቱ በተፈፀመ በ24 ሰዓታት ውስጥ በሁለቱ አካላት ከፍተኛ ወታደራዊ ኮማንደሮች መካከል ግንኙነት እንዲፈጠርና በሂደቱ ላይ በአምስት ቀናት ውስጥ ውይይት እንዲያደርጉ ይደነግጋል፡፡
ቀጥሎም ከኮማንደሮቹ ስምምነት በኋላ ባሉት 10 ቀናት ውስጥ ለከባድ መሳርያዎች ቅድሚያ ተሰጥቶት የትጥቅ ማስፈታቱ ተግባር እንዲጀመር ይላል፡፡ ትንንሽ መሳርያዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የትጥቅ አፈታት ሂደቱ፣ ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ባሉት 30 ቀናት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ በሰነዱ ላይ ሰፍሯል፡፡
በሰነዱ አንቀጽ 3 ላይ ደግሞ “በትግራይ ክልል ሕዝባዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንዲሁም የከተማዋን ነዋሪዎች ደህንነት ለመጠበቅ የፌዴራል ኃሎች መቀሌ ከተማ እንዲገቡ ፓርቲዎቹ ተስማምተዋል” ይላል፡፡ ለዚህም ተግባራዊነት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች የፌዴራል ተቋማት፣ የሁለቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች በሚያደርጉት ግልጽ ግንኙነት አማካኝነት በሰላማዊና በተቀናጀ መልኩ በፍጥነት መቀሌ መግባት እንዳለባቸው ይደነግጋል፡፡
የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ከትላንት በስቲያ እሁድ ታህሳስ 16/2015 ዓ.ም ባደረጉት ግምገማ፣ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶርያ የተደረሰው የሰላም ስምምነት አተገባበር “ዘግይቷል” ማለታቸው የሚታወስ ነው፡፡
ከዚህ ግምገማ ማግስት፣ ማለትም ትላንት ታህሳስ 17 የፌዴራሉ መንግስት ልዑካን በመቀሌ ካደረጉት ጉብኝት በኋላ ግን ፈጣን ለውጦችን መመልከት ተችሏል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የልዑካን ቡድኑን ወደ መቀሌ መላካቸው “መንግስት (በሰላም ስምምነቱ) ወደፊት ለመግፋት ያለውን ቁርጠኝነት ያረጋግጣል” ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፣ “እንቅፋቱ እምነት ማጣት ነበር፤ ይህንን እንደገና ለማቀጣጠል ደፍረን ተነስተናል” በማለትም አክለዋል።
የፌዴራል መንግስቱ ልዑካን መቀሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የተቀበሏቸው የሕወሓት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው “ከልዑካን ቡድኑ አባላት ውስጥ አንዳቸውም ጠባቂዎቻቸውን ይዘው አለመምጣታቸው ትግራይ ለሰላም ስምምነቱ ባላት ቁርጠኝነት ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ ነው” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ጽፈዋል፡፡
ፍሬያማ ውይይት እንዳደረጉ እና ጠቃሚ መግባባት ላይ እንደደረሱም ነው አቶ ጌታቸው ገልፀዋል፡፡