ሰሜን ኮሪያ ዛሬ ሰኞ በርካታ ትናንሽ ድሮኖችን ወደ ደቡብ ኮሪያ የአየር ክልል ውስጥ ማሰማራቷን የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣኖች ተናገሩ።
ሰሜን ኮሪያ የወሰደችው እርምጃ ደቡብ ኮሪያ የራሷን ሰው አልባ የስለላ የጦር አውሮፕላኖች አሳስቢ ወደ ሆነው የሰሜን ድንበሯ እንድታሰማራ ያስገደዳት መሆኑም ተመልክቷል።
ደቡብ ኮሪያ ተዋጊ ጀቶችና አጥቂ ሂሊኮፕተሮችዋ የሰሜን ኮሪያዎቹን ወራሪ ድርኖቾ ለማጥቃት ሙከራዎችን ያደረገች ቢሆንም አንዳቸውንም መታ መጣል አለመቻሏን የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ለሪፖርተሮች መናገራቸው ተዘግቧል።
ይህ ክስተት ደቡብ ኮሪያ ከሰሜን ኮሪያ ጥቃት ራሷን የመከላከል ብቃት ከጥያቄ ውስጥ ያስገባ ክስተት መሆኑም ተመልክቷል።
ይሁን እንጂ ከሰላዩቹ የሰሜን ኮሪያ ድሮኖች አንዱ ብቻ ወደ ሰሜን ኮሪያ የተመለሰ መሆኑ ሲነገር ሌሎች አራቱ የገቡበት አለመታወቁን አንድ የደቡብ ኮሪያ ወታደራዊ ባለሥልጣን ለሪፖርተሮች መናገራቸው ተመልክቷል።
የሰሜን ኮሪያ ድሮኖች የጦር መሳሪያ የተገጠመላቸው መሆኑ ባይታወቅም የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ግን ድሮኖቹ ሁለት ሜትር ያህል የሚደርስ ክንፍ ያላቸው እጅግ ጥቃቅን መሆናቸውን ተናግረዋል።
እኤአ 2014 ውስጥ ሰሜን ኮሪያ በአራት የተለያዩ ጊዜያት ሰው አልባ የቅኝት አውሮፕላኖችን መላክዋ የተገለጸ ቢሆንም የአየር ክልልን ጥሳ ስትገባ ከአምስት ዓመት በኋላ ይህ የመጀመሪያው መሆኑ ተዘግቧል።