በዩናይትድ ስቴትስ ምስራቃዊ ክፍሎች ኃይለኛ በረዶ እና ቅዝቃዜ በተከሰተበት ወቅት የክረምቱ አውሎ ንፋስ በገና ቀን ባስከተለው አደጋ በትንሹ 32 ሰዎች መሞታቸው እና ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊጨምር እንደሚችል የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።
እጅግ ግዙፍ የሆነው ቅዝቃዜና ዝናብ ያዘለው ነፋስ ከሰሜን የአገሪቱ አካባቢዎች እስከ ደቡብና ምስራቅ የአገሪቱ ከፍሎች እንዲሁም ከዩናይትድ ስቴትስ ባህረ ሰላጤ አንስቶ እስከ ሰሜን ምስራቅ የባህር ዳርቻ ድረስ መንቀሳቀሱ ተገልጿል፡፡
በዚህ የዓመቱ ክፍለ ጊዜ ከተለመደው የሙቀት መጠን ውጭ ከዜሮ በታች ወርዶ የቀዘቀዘውና እጅግ ከባድ የሆነው የአየር ጠባይ እስከ ማክሰኞ ድረስ እንደሚዘልቅ የብሄራዊ የአየር ትንበያ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
ከባድ ነፋስ የቀላቀለው ዝናብ 60 ከመቶ በሚሆነው ዩናይትድ ስቴትስ ህዝብ ላይ ተጽእኖውን ያሳረፈ ሲሆን የኃይል አቅርቦት መስመሮች ላይ ጉዳት በማድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ በረራዎችን ማስተጓጎሉ ተነግሯል፡፡
ብሄራዊ የአየር ትንበያ አገልግሎት ባለሥልጣናት በቡፋሎ የናያግራ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ባላፈው እሁድ ማለዳ የጣለውና የተከመረው በረዶ ሲለካ ከአንድ ሜትር በላይ እንደነበረ አስታውቀዋል፡፡
በሺዎች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥና ዓለም አቀፍ በረራዎች መሰረዛቸውንም በረራዎችን የሚከታተለው ፍላይት አዌር የተባለው ድርጅት አስታውቋል፡፡