በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ ህብረት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ በድጋሚ ጠየቀ


የአውሮፓ ህብረት ባንድራ
የአውሮፓ ህብረት ባንድራ

የአውሮፓ ኅብረት በኢትዮጵያ መንግስትና በህወሃት መካከል የተፈረመውን የሰላም ስምምነት አድንቆ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ እንዲወጣ በድጋሚ ጠይቋል።

ኅብረቱ ትናንት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው የኢትዮጵያ መንግስትና ህወሃት የሰላም ስምምነቱን መፈረማቸውን እንዲሁም ያንን ተከትሎ የሁለቱ ወገን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦች የስምምነቱን አፈጻጸም በተመለከተ ተገናኝተው መግባባት ላይ መድረሳቸው በኢትዮጵያ ሰላምና እርቅን ለመፍጠር ወሳኝ እርምጃ ነው ብሏል።

የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ጠንካራ አመራር ያስፈልጋል ያለው የኅብረቱ መግለጫ፣ ተኩስ አቁሙ በሁለቱም ወገኖች መተግበሩን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግና ይህም ለእርቅና መልሶ ግንባታ ጥርጊያ መንገድ ይከፍታል ብሏል።

እስከአሁን የታየውን አዎንታዊ ሂደት ያደነቀው ኅብረቱ ስምምነቱን በተግባር ለመተርጎም ለሚደረገው ጥረት ድጋፍ እንደሚሰጥም አስታውቋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው የሰብዓዊ ሁኔታ የተቀናጀ ሥራ ያስፈልገዋል ያለው መግለጫው፣ ያልተገደበ ሰብዓዊ ተደራሽነትና የመሠረታዊ አገልግሎቶች እንደገና መመለስ እጅግ አስፈላጊ ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ ያቀረበው የአውሮፓ ኅብረት፣ ከ 20 ዓመት በፊት በአልጀርስ የተፈረመውን የኢትዮጵያና የኤርትራን የሰላም ስምምነት በማስታወስ፣ ኤርትራ ጦሯን “በአፋጣኝና በአስቸኳይ” ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ ጥሪውን በድጋሚ አሰምቷል።

XS
SM
MD
LG