በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም ዋንጫ ባልተፈቀደለት ሠው የመነካቱን ጉዳይ ፊፋ ሊመረምር ነው


በካታር ሉሳሊ ስታዲየም በአርጀንቲና እና ፈረንሳይ መካከል የተካሄደው የዓለም ዋንጫ ሲጠናቀቅ፣ በስተቀኝ የሚታየው ኑስረት ጉክቸ እጁን በአርጀንቲናው ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ ትከሻ አድርጎ ይታያል -ታህሳስ 18, 2022
በካታር ሉሳሊ ስታዲየም በአርጀንቲና እና ፈረንሳይ መካከል የተካሄደው የዓለም ዋንጫ ሲጠናቀቅ፣ በስተቀኝ የሚታየው ኑስረት ጉክቸ እጁን በአርጀንቲናው ተጫዋች ሊዮኔል ሜሲ ትከሻ አድርጎ ይታያል -ታህሳስ 18, 2022

ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አንድ የታዋቂ ሰዎች ምግብ አብሳይ ዋንጫውን ይዞ የመታየቱን ጉዳይ ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በመመርመር ላይ መሆኑን አስታወቀ።

ታዋቂው ቱርካዊ ምግብ አብሳይ ኑስረት ጉክቸ ወይም በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት በሚታወቅበት ስሙ ‘ሳልት ቤ’ ባለፈው እሁድ ከፍጻሜ ጨዋታው በኋላ እንዴት ወደ ሜዳው እንደገባና ዋንጫውን ለመያዝ እንደበቃ ምርመራ ይደረጋል ሲል ፊፋ አስታውቋል።

በፊፋ ድህረ ገጽ ላይ እንደሰፈረው ዋንጫው በዓለም ትልቁ የስፖርት ምልክት ሲሆን፣ መነካት የሚችለው በተወሰኑ ሰዎች ብቻ ነው። የቀድሞ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዎች እና የአገራት መሪዎች መንካት ከሚፈቀድላቸው ጥቂቶቹ ናቸው።

ግለሰቡ እንዴት ወደሜዳው ዘልቆ እንደገባ ተመርምሮ አስፈላጊው የውስጥ እርምጃ ይወሰዳል ሲል ፊፋ ማስታወቁን ኤ.ኤፍ.ፒ ዘግቧል፡፡

በሚያበስለው ምግብ ላይ በተለየ ቄንጥ ጨው በመንስነስ የሚታወቀው ‘ሳልት ቤ’ ባለፈው እሁድ የአርጄንቲና ተጨዋቾች በያዙት የዓለም ዋንጫ ላይ ጨው እንደሚነሰንስ ዓይነት ምልክት አሳይቷል። በኋላም ዋንጫውን ተቀብሎ ከፍ አድርጎ ይዟል። 50 ሚሊዮን ለሚሆኑ የኢንስታግራም ተከታዮቹ ፎቶውንና ቪዲዮውን አጋርቷል።

ቱርክ፣ ኢስታንቡል ውስጥ በትንሽ ልኳንዳ ሥራ የጀመረው የ 39 ዓመቱ ‘ሳልት ቤ’ሳልት ቤ፣ አሁን ከ 20 በላይ ቅንጡ ምግብ ቤቶች በዓለም ዙሪያ ያሉት ሲሆን 70 ሚሊዮን ዶላር ሃብት እንዳለው ይነገራል።

XS
SM
MD
LG