የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክርቤት በሚየንማር ያለው ሁከት እንዲቆምና አገሪቱን በመምራት ላይ ያለው ሁንታ ኦንግ ሳን ሱ ቺን እና ፕሬዝደንት ዊን ማይንትን ጨምሮ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲለቅ ትናንት ባወጣው የውሳኔ ሃሳብ ጠይቋል።
የፀጥታው ም/ቤት በተጨማሪም በሚየንማር ያለው ሁኔታ በደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች ማኅበር የወጣውን ባለ አምስት ነጥብ ስምምነት በአስቸኳይና በተጨባጭ ተግባራዊ እንዲያደርግ እና የሚየንማርን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ መሻት እንዲያከብር ጠይቋል።
ከሰባ ዓመታት በኋላ በሚየንማር ጉዳይ ላይ የወጣውን የውሳኔ ሃሳብ 21 አገሮች ሲደግፉት፣ ሶስት ሀገሮች ደግሞ ድምፀ ተአቅቦ አድርገዋል። ድምፀ ተአቅቦ ያደረጉት ቻይና ህንድና ሩሲያ መሆናቸው ታውቋል።
ቻይናና ሩሲያ በሚየንማር ቀውስ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንዳይወስድ ሲቃወሙ ቆይተዋል።
ቻይና የፀጥታው ምክርቤት ከውሳኔ ሃሳብ ይልቅ መግለጫ ቢጤ እንዲያወጣ ትመርጥ ነበር። ሩሲያ በበኩሏ የሚየንማር ችግር እንደ ከባድ ጉዳይ በፀጥታው ምክርቤት መታየት አይገባውም ባይ ነች።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን እ.አ.አ በ1948 በተቀላቀለችው በሚየንማር ፣ ወይም በቀድሞ ስሟ በርማ ላይ የፀጥታው ምክርቤት ውሳኔ ሲያወጣ የትናንቱ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።