ወታደራዊ መፈንቅለ-መንግስት ማክሸፏንና የፕሬዝደንት አዳማ ባሮውን አስተዳደር ለመገልበጥ አሲረዋል የተባሉ አራት ወታደሮችን በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ጋምቢያ ዛሬ አስታውቃለች።
የጋምቢያ መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ትናንት ማክሰኞ በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ ነው አራቱ ወታደሮች በቁጥጥር ሥር የዋሉት።
“አንዳንድ የጋምቢያ ወታደሮች በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠውን መንግስት ሊገለብጡ አሲረው ነበር” ብሏል በመንግስት ዛሬ የወጣው መግለጫ።
2.5 ሚሊዮን ሕዝብ ባላትና ሙሉ ለሙሉ በሚባል በሴኔጋል በተከበበችው ትንሿ ምዕራባዊ አፍሪካ አገር መንግስት ግልበጣ የተለመደ አይደለም።
ሮይተርትስ ዛሬ ከስፍራው የመንግስትን መግለጫ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ተባባሪ ናቸው የተባሉ ሶስት ሌሎች ሰዎችን ሰራዊቱ በማደን ላይ ነው።
በቀድሞው የሴኔጋል ፕሬዝደንት ያህያ ጃመህ ወታደራዊ አማካሪ የተመራ ነው የተባለ መፈንቅለ-መንግስት በፕሬዝደንት አዳማ ባሮው ላይ አሲረዋል የተባሉ 8 የቀድሞው የጋምቢያ ወታደሮች ከሶስት ዓመት በፊት በእስር ተቀጥተዋል።