በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሶማሊያ በኤርትራ ስልጠና ላይ የነበሩ ወታደሮቿን መመለስ ጀመረች


ፋይል - የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ኤርትራን በጎበኙበት ወቅት
ፋይል - የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ኤርትራን በጎበኙበት ወቅት

በኤርትራ ስልጠና ላይ የነበሩ የሶማሊያ ወታደሮችን የያዘ አውሮፕላን በሞቃዲሹ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ መድረሱን የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ዛሬ አስታውቀዋል።

ሚኒስትሩ አብዱልቃድር ሞሃመድ ኑር ለቪኦኤ ሶማሊኛ ክፍል እንዳረጋገጡት፣ የመጀመሪያው ዙር ወታደሮችን የያዘ አውሮፕላን ሞቃዲሹ መድረሱንና፣ በሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮቹን የመመለሱ ሥራ በመጪ ቀናቶች ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል።

“ጥሩ ሞራል ላይ ይገኛሉ፣ ደስተኞች ናቸው፣ የሞቀ አቀባበልም ተደርጎላቸዋል” ሲሉ አክለዋል ሚኒስትሩ።

የሶማሊያ መንግስት 5ሺህ የሚሆኑ ወታደሮቹን በኤርትራ እንዲሰለጥኑ አድርጓል። አንዳንዶቹ ወታደሮች በልዩ ተዋጊ ሃይል፣ ሌሎቹ ደግሞ በባህር ሃይል እና በአየር ሃይል መስክ ሰልጥነዋል ተብሏል።

ዛሬ በመጀመሪያው ዙር ምን ያህል ወታደሮች እንደተመለሱ ባለስልጣናት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሩ አብዱልቃድር ሞሃመድ ኑር እንዳሉት የወታደሮቹ መመለስ በአል-ሻባብ ላይ የሚደረገውን ዘመቻ ያጠናክረዋል።

ኻዋሪጅ ሲሉ የጠሯቸውን የአል-ሻባብ ተዋጊዎችን ለመደምሰስ ጉልበት ይሆኑናል ሲሉ ተደምጠዋል ሚኒስትሩ።

የአገሪቱ ፕሬዝደንት ሃሳን ሼክ ሞሃመድ በኤርትራ ያሉ ወታደሮቻቸው በዚህ ወር ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚጀምሩ ትናንት አስታውቀው ነበር። ፕሬዝደንቱ ወታደሮቹን ኤርትራ ድረስ በመሄድ ሁለት ግዜ ጎብኝተዋቸዋል።

ለስልጠና ኤርትራ የነበሩት የሶማሊያ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ሳይሳተፉ አይቀርም የሚል ያልተረጋገጠ ወሬ ለወራት ሲሽከረከር መቆየቱ የሶማሊያውን መንግስት ከወታደሮቹ ቤተሰቦች ጋር ቅራኔ ውስጥ ከቶ ነበር።

የቪኦኤው ሶማሊኛ ክፍል ወታደሮቹ ወደ ትግራይ ስለመላካቸው ምንም ማስረጃ እንዳላገኘ በሪፖርቱ ጠቁሟል፡፡ ወታደሮቹ ወደ ኤርትራ የተላኩት ከሶስት ዓመት በፊት ነበር።

XS
SM
MD
LG