በርካታ ጥሬ ገንዘብ በቤታቸው ተገኝቷል በሚል የፖለቲካ ህይወታቸው አደጋ ላይ ወድቆ የነበሩት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሰሪል ራማፎሳ የፓርቲያቸው የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ (ኤ ኤን ሲ) መሪ ሆነው በድጋሚ ተመርጠዋል።
በደቡብ አፍሪካ ላለፉት 30 ዓመታት ገዢ ፓርቲ የሆነውን ኤ.ኤን.ሲ መሪነት ማረጋገጣቸውም፣ በድጋሚ የሃገሪቱ ፕሬዝደንት ሆነው ለመመረጥ ጥርጊያ መንገድ ይከፍትላቸዋል ሲል ኤ.ኤፍ.ፒ ከስፍራው ዘግቧል።
የ 70 ዓመቱ ባለጸጋና የፖለቲካ ሰው ከአምስት ዓመታት በፊት የፓርቲው መሪ ሆነው ሲመረጡ እንደነበረው ጠንካራ ድጋፍ ያላቸው አይደሉም ተብሏል። በደቡብ አፍሪካ የነበረውን የዘር መድሎ ለመታገል በኔልሰን ማንዴላና አጋሮቻቸው የተመሠረተው ኤ.ኤን.ሲ ውስጥ መከፋፈል መፈጠሩ ተገልጿል።
ከአራት ዓመታት በፊት ለፕሬዝደንትነት ሲመረጡ ለአገሪቱ አዲስ ተስፋ ይዘው ቢነሱም፣ የኢኮኖሚ ድቀቱና በእርሳቸው ላይ የሚነሳው የገንዘብ ቅሌት ክስ የነበራቸውን ተቀባይነት ጎድቶታል።
በአገሪቱ ፓርላማ የተቋቋመ ገለልተኛ መርማሪ ቡድን ከራማፎሳ የገጠር መዝናኛ ቤት ተሠረቀ የተባለው ግማሽ ሚሊዮን ዶላር የሚሆን ጥሬ ገንዘብ በታክስ ሪፖርት ላይ ያልታየና ምንጩ የማይታወቅ ነው፣ ራማፎሳ የእምነት ማጉደል ሳይፈፅሙ አይቀርም በማለት ቀርበው መልስ እንዲሰጡ ባለፈው ወር ባወጣው ሪፖርት ጠይቆ ነበር።
በፓርላማው አፈ-ጉባኤ የተቋቋመው አጣሪ ቡድን ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ጥሬ ገንዘብ በራማፎሳ የገጠር ቤት ሶፋ ሥር ከተደበቀበት መሠረቁን ነገር ግን ፕሬዝደንቱ ክስተቱን ሪፖርት ሳያደርጉ ማለፋቸውን ባለፈው ወር አስታውቋል።
ፓርቲያቸው ኤ.ኤን.ሲም ሆነ ብሄራዊ ሸንጎው ግን በእርሳቸው ላይ ሊካሄ የነበረውን የክስ ሂደት ባለፈው ሳምንት አስቁሞታል።
ከገጠር የእረፍት ቤታቸው ተሰረቀ የተባለውን ገንዘብ 20 ጎሾችን ለአንድ ሱዳናዊ ሸጠው ያገኙት እንደሁነ ራማፎሳ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል።