የትዊተር ባለቤት ኤሎን መስክ ከሐሙስ ጀምሮ አግደዋቸው የነበሩትን የጋዜጠኞች ገፅ እንደሚመልሉ ቅዳሜ ጠዋት በትዊተር አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት አስታውቀዋል። መስክ ይህን መልዕክት ካስተላለፉ ከጥቂት ደቂቃዎች በኃላም የአሜሪካ ድምፅ ዋና ብሄራዊ ዘጋቢ ስቲቭ ኸርማንን ጨምሮ ታግደው የነበሩ ጋዜጠኞች ገፆቻቸው ተመልሰውላቸዋል።
መስክ ገፆቹን ያገዱበት ምክንያት ጋዜጠኞቹ የግል ጄት አውሮፕላናቸው የሚገኝበትን ቦታ በመግለፃቸው እና ይህም አንደኛው ልጃቸው ላይ ክትትል እና ትንኮሳ እንዲደርስበት በማድረጋቸው ነው ብለዋል። ሆኖም ገፃቸው የታገደባቸው ግዜጠኞች ስለመስክ እና "ኤሎን ጀት" ስለተሰኘው አካውንታቸው ቢዘግቡም፣ አውሮፕላናቸው የሚገኝበትን ቦታ የሚመለከት መረጃ በትዊተር ገፃቸው አላስተላለፉም። መረጃው ግን በሌሎች ደህረገፅ ላይ በይፋ የሚገኝ ነው።
የትዊተር ገፆቹ መዘጋት በበርካታ ጋዜጠኞች፣ የመብት ተሟጋች ቡድኖች እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሬክ አርብ እለት በሰጡት መግለጫ "እርምጃው በዓለም ዙሪያ ባሉ ጋዜጤኞች ላይ ሳንሱር፣ አካላዊ ስጋት እና ከዛም የከፉ አደጋዎች በተጋረጡበት ግዜ መፈፀሙ አደገኛ አካሄድ ይፈጥራል" ብለዋል። አክለውም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት 'በዘፈቀደ እገዳው' መረበሹን አስታውቀዋል።
የአውሮፓ ህብረትም በተመሳሳይ መልኩ እገዳው እንዳሳሰበው አስታውቋል። የህብረቱ ኮሚሽን የእሴቶች እና ግልፅነት ምክትል ፕሬዝዳንት ቬራ ጆርቫ በትዊተር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት እገዳዎቹ አሳሳቢ መሆናቸውን ገልፀው "የአውሮፓ ህብረት ዲጂታል አገልግሎት የሚዲያ ነፃነትን እና መሰረታዊ መብቶችን ማክበርን ይጠይቃል። የሚዲያ ነፃነት ህጉም ይህን ያስከብራል" ብለዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ስጋቱን የገለፀው የጋዜጤኞች መብት ተሟጋች ኮሚቴም ጋዜጠኞች በስራቸው ምክንያት በተወሰደ የበቀል ርምጃ መታገዳቸውን ገልፆ "ይህ ጋዜጠኞች ያለ ፍርሃትና ያለ በቀል ዜና የመዘገብ መብታቸውን የሚጥስ ነው" ብሏል።
መስክ የጋዜጠኞቹ የትዊተር ገፆች እንዲመለሱ ለመወሰን የትዊተር ምርጫ ያካሄዱ ሲሆን 59 ከመቶ የሚሆኑ መላሾች ገፆቹ በአስቸኳይ እንዲመለሱ ጠይቀዋል። መስክ ውጤቱን አስመልክቶ በትዊተር ገፃቸው መፃፉት መልዕክትም "ህዝቡ ተናግሯል" ብለዋል።