በቱኒዚያ ዛሬ እየተካሄደ ባለው የፓርላማ ምርጫ ቱኒዚያውያን የመምረጥ ፍላጎታቸው አነስተኛ ሆኖ ተስተውሏል። አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሬዝዳንት ካያስ ሰኢድ ወደ አንድ ሰው አገዛዝ የሚያደርጉት ጉዞ ማስፈፀሚያ ነው ሲሉ ባወገዙት ምርጫ አልተሳተፉም።
ቱኒዚያዊው አትክልት ሻኝ መሀመድ ቡአዚዚ የአረብ አብዮትን በቀሰቀሰ የተቃውሞ እርምጃ እራሱን ካቃጠለ ከ12 ዓመታት በኃላ እየተካሄደ ባለው ምርጫ አዲስ የፓርላማ አባላት የሚመረጡ ቢሆንም ህግ አውጪዎቹ በመንግስት ፖሊሲ ላይ የሚኖራቸው ተፅእኖ እምብዛም መሆኑ ተገልጿል።
ሮይተርስ ቱኒዝ ውስጥ የሚገኙ ስድስት የምርጫ ጣቢያዎችን ለሁለት ሰዓታት ተዟዙሮ የተመለከት ሲሆን ጋዜጠኛው 20 ሰዎች ብቻ ድምፃቸውን ሲሰጡ ማየቱን ዘግቧል።
በፕሬዝዳንት ሰኢድ የተሾሙት የምርጫ ኮሚሽን አባላትም፣ የምርጫ ጣቢያዎች ከተከፈተ በኃላ ባሉት 2 ሰዓታት ውስጥ 270 ሺህ ሰዎች ወይም ድምፅ መስጠት ከሚችሉ ዘጠኝ ሚሊየን መራጮች ውስጥ ሶስት ከመቶ ብቻ የሚሆኑት ድምፅ መስጠታቸውን አስታውቀዋል።
የቱኒዚያ ምርጫ የሚካሄደው በሀገሪቱ ድህነትን እያባባሰ ባለው እና በርካቶች በህገወጥ አዘዋዋሪዎች መርከብ ተሳፍረው ወደ አውሮፓ እንዲሰደዱ እያስገደደ ባለው የኢኮኖሚ ቀውስ ወቅት መሆኑ ተዘግቧል።