በሰሜን ማሊ ቲምቡክቱ ከተማ በሰላም አስከባሪ ኃይሎች ላይ በደረሰ ጥቃት ከናይጄሪያ የመጡ ሁለት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰላም አስከባሪዎች መገደላቸውን እና አራት መቁሰላቸውን የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ። አርብ እለት በደረሰው ጥቃት አንድ የማሊ የፀጥታ ኃይል አባል መገደሉንም የመንግስታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጨምሮ አስታውቋል። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ እንደተናገሩት፣ ከተገደሉት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች መካከል አንዷ ሴት ነች።
የመንግስታት ድርጅቱ ዋና ፀሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ እና የፀጥታው ምክር ቤት ጥቃቱን አጥብቀው አውግዘዋል።
ምክር ቤቱ አክሎ በተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ማቀድ፣ መምራት፣ መደገፍ ወይም በድርጊቱ ላይ መሳተፍ የጦር ወንጀልን ሊያመለክት እንደሚችል አሳስቧል።
እ.አ.አ በ2012 ከተቀሰቀሰው ህዝባዊ አመፅ ጀምሮ ማሊ ውጥንቅጥ ውስጥ የገባች ሲሆን አድማ ያደረጉ ወታደሮች ፕሬዝዳንቱን ከስልጣን ካስወገዱ በኃላ የጂሃዲስት አመፅ ያስከተለ ከፍተኛ የስልጣን ክፍተት ፈጥሯል።