በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የትግራዩ ግጭት ረገብ ሲል የኦሮምያው ተባብሷል


የትግራዩ ግጭት ረገብ ሲል የኦሮምያው ተባብሷል
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:32 0:00

የትግራዩ ግጭት ረገብ ሲል የኦሮምያው ተባብሷል

በአንድ ወቅት በአፍሪካ ፈጣን እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገሮች አንዱ የተባለላትን የምጣኔ ሃብቷን ለማንሰራራትና መንግሥት በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የተጣለበትን ማእቀብ ለማስነሳት ጥረት እያደረገ ባለበት ኢትዮጵያ፤ አንድ አውዳሚ ጦርነት እየከሰመና ሌላው እየከፋ መሆኑ ተዘገበ።

"በያዝነው ሳምንት ዋሽንግተን ላይ እየተካሄደ ባለው የዩስ-አፍሪካ የመሪዎች ጉባኤ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው ወር በመንግስታቸው እና በትግራይ ክልል ባለስልጣናት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማስተዋወቅ ጥረት እያደረጉ ባሉበት እንኳን ሳይቀር በኦሮሚያ ክልል የሚታየው ያለመረጋጋት እየተባባሰ ይመስላል።” ብሏል ዘገባው።

የ120 ሚሊዮን ህዝብ መኖሪያ እና በሕዝቧ ቁጥር በአፍሪካ ሁለተኛዋ የሆነችው አገር በጎሳ ቡድኖች እና በታጠቁ አጋሮቻቸው መካከል በተፈጠረው ውጥረት ክፉኛ እየተናጠች ትገኛለች። በሃገሪቱ በቁጥራቸው ትልልቆቹ የኦሮሞ እና የአማራ ብሄረሰቦች በግድያዎች አንዱ ሌላውን ተጠያቂ እያደረጉ ነው።

የቴሌኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ብዙ ጊዜ በሚቋረጥበት እና ነዋሪዎች ብንናገር ይደርስብናል የሚሉትን በመስጋት ከመናገር በሚቆጠቡበት በክልሉ በሚፈጸሙ ጥቃቶች የሞቱት ሰዎች ቁጥር በውል ያለመታወቁን የጠቀሰው ዘገባ አያይዞም ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ በክልሉ የሚኖሩ ሰዎች ባለፉት ሳምንታት የተፈጸመውን አሰቃቂ ጥቃት አስመልክት አስተያየት ያደረሱት መሆኑን አመልክቷል።

በኦሮሚያዋ የኪራሙ ወረዳ ነዋሪ የሆኑ አንድ እማኝ ከህዳር 15 አንስቶ ከተገደሉት 34 ሰዎች መካከል አባቱ እና የአጎታቸው ልጅ እንደሚገኙበት ተናግረዋል። በኦሮሚያ ክልል መንግስት ስር ያሉ ወታደሮች እንደሚገኙበት የደንብ ልብሳቸውን አይቻለሁ ሲሉ መክሰሳቸውን ዘግቧል።

"ይህ ሁሉ የተጀመረው በአንድ የአካባቢው ሚሊሻ እና በአንድ የኦሮሚያ ክልል ልዩ ኃይል አባል መካከል በተፈጠረ ግጭት ነው" ያሉት አስተያት ሰጭ “ልዩ ኃይሉ የአማራ ማህበረሰብ አባል የሆነውን ሚሊሻ ከገደለ በኋላ ለአንድ ሳምንት የቀጠለ ግድያ ተፈጽሟል” ማለታቸውን፣ከዚያም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢውን ትተው መሰደዳቸው አመልክተዋል።

የኪራሙ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የኦሮሞ ተወላጅ በበኩላቸው ፋኖ ተብሎ የሚጠራው የአማራ ታጣቂ ቡድን በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እና ግድያ ፈጽሟል ሲሉ ይከሳሉ። ከ12 በላይ አስከሬኖችን ማየታቸውን እና አራቱን መቅበራቸውን ይናገራሉ።

"ይህ የሚሊሺያ ቡድን ህዝባችንን እየገደለ፣ መንደሮችን እያቃጠለ እና ያለንን ሁሉ እየዘረፈ ነው" ሲል ዱጋሳ ፈይሳ የተባሉ ሰው እንደነገሩት የዘገበው አሶሽዬትድ ፕሬስ “የመንግስት ሰራተኛ፣ ፖሊስ ወይም መምህራን ሊሆኑ ይችላሉ። “ባገኙት ሰው ላይ ይተኩሳሉ።” ማለታቸውንም አክሏል።

የኦሮሞና የአማራ ብሔረሰብ አባላት ለዓመታት አብረው መኖራቸውን ነገር ግን ከዚህ ቀደም ይህን መሰል ግጭት አይተው እንደማያውቁም መናገራቸውን ጠቅሷል።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በኦሮሚያ የተከሰተውን አስከፊ ሁከት አስመልክቶ የተናገሩ የጊዳ አያና ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪም የአማራ ፋኖ ተዋጊዎችን ተጠያቂ ማድረጋቸውን ዘግቧል።

“በአካባቢያችን ያሉ ዜጎች እየተገደሉ፣ እየተፈናቀሉና እየተዘረፉ ነው። ይህ ቡድን በጣም የታጠቀ በመሆኑ መከላከያ ከሌላቸው አርሶ አደሮች አቅም ጋር አይመጣጠንም” ያሉት አቶ ጌታሁን ቶሌራ ወረዳቸው በአሁኑ ወቅት በአቅራቢያው ከሚገኙ ሌሎች ወረዳዎች የተሰደዱ ቁጥራቸው 31,000 የሚደርሱ ሰዎችን ማስጠለሉን እና አሁንም ከቤት ወደ ቤት እየተዘዋወሩ አስከሬን በማንሳት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት በኦሮሚያ ስለተፈጸሙት ግድያዎች አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆኑ መቅረታቸውን እና እስካሁንም በግልፅ ያለመናገራቸውን ዘገባው ይዘረዝራል።

አያይዞም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ሳምንት ሲናገሩ አንዳንድ “ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው ጠላቶች” ያሏቸው አገሪቱን ለማተራመስ እየጣሩ ናቸው ማለታቸውን ጠቅሷል። ጉዳዩን አስመልክቶ ዝርዝር መግለጫ ግን አልሰጡም፣ ነው ያለው።የአለም አቀፍ ቀውሶች ተከታታዩ ክራይሲስ ግሩፕ ተንታኝ ዊሊያም ዴቪሰን “የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች፣ የኦሮሞ ታጣቂዎች እና የአማራ ሚሊሻዎች ኦሮሚያ ውስጥ እየተፋለሙ ነው” ማለታቸውንም ዘግቧል።

ግድያዎቹን በመቃወም ከጥቂት ቀናት በፊት በአንዳንድ አካባቢዎች ሰልፎች ሲካሄዱ፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚገኙ 10 ዞኖች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን እና በተደጋጋሚ ግድያዎቹ በተፈጸሙባቸው በእነኚህ አካባቢዎች የመንግስት ኃይሎች እና እንዲሁም የአማራ እና የኦሮሞ ታጣቂዎች መኖራቸውን ማረጋገጡን ዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ እና እናት ፓርቲ ለተጎዱት ማህበረሰቦች የተሻለ ጥበቃ እንዲደረግ የጠየቁ ሲሆን፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን አንድ ከፍተኛ ባለስልጣን በበኩላቸው የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቃቸውን አመልክቷል።

የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረሱ ጃዋር መሀመድም በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በሰጡት አስተያየት ኪራሙ፣ ሆሮ ጉዱሩ፣ ኩዩ እና ዋራ ጃርሶ በተባሉት የተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች 350 ሰዎች መገደላቸውን እና “ባለፉት 48 ሰዓታት ውስጥ” ከ400 ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን መናገሩን ዘግቧል።

"መንግስት ምንም እንዳልተፈጠረ ማስመሰሉን ማቆም አለበት" ሲል በፌስቡክ ገፁ ያሰፈረው ጃዋር “ጦርነቱ ሰላማዊ ዜጎችን የጨመረ የወል ግጭቱ እየሆነ ነው። በፍጥነት ካልተያዘ ወደ ሁለቱ ክልሎች ሌሎች አካባቢዎችም ሊዛመት ይችላል።” ማለቱን የአሶሽዬትድ ፕሬሱ ዘገባ ጠቅሷል።

/ በአሶስዬትድ ፕረስ የተጠናቀረውን ዘገባ ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ/

XS
SM
MD
LG