በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩኤስ-አፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ነገ ይጀመራል


የዩኤስ-አፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ነገ ይጀመራል
please wait

No media source currently available

0:00 0:07:35 0:00

የዩኤስ-አፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ነገ ይጀመራል

ነገ ማክሰኞ ለሚከፈተው ዩኤስ-አፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ለመሳተፍ የአህጉሪቱ መሪዎች ዋሽንግተን ዲሲ በመግባት ላይ ናቸው። በዚህ ጉባኤ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ኅብረት የቡድን 20 አገራት ቋሚ አባል እንዲሆን አሜሪካ ድጋፍ እንደምትሰጥ ያስታውቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዝደንት ጆ ባይደን 50 ከሚሆኑ የአፍሪካ መሪዎችና የልዑካን ቡድናቸው፣ በአፍሪካ የግል ኩባንያ ባለቤቶች እንዲሁም የዳያስፖራ ማኅበረሰብ ተወካዮች ጋር ስብሰባ ይቀመጣሉ።

በሌላ በኩል በአሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ ማኅበራትና ግለሰቦች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄዳል ያሉትን ሁከት በመጥቀስ፣ ፕሬዝደንት ባይደን የኢትዮጵያን ፕሬዚደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ለጉባኤው መጋበዛቸውን በመቃወም ደብዳቤ ጽፈዋል፣ ግብዣው እንዲሰረዝም ጥሪ አድርገዋል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴንም ሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድን እንዳያገኙም ጥሪ አድርገዋል።

የወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር የሆኑት የሴኔጋሉ ፕሬዝደንት ማኪ ሳል እና የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሰሪል ራማፎሳ በጠየቁት መሠረት፣ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ኅብረቱ የቡድን 20 ሀገሮች ማኅበር ቋሚ አባል እንዲሆን ያላቸውን ድጋፍ እንደሚያስታውቁ የዋይት ሃውስ አማካሪ የሆኑት ጀድ ዴቨርሞንት ተናግረዋል።

ከአፍሪካ ሀገሮች ውስጥ እስከ አሁን የቡድን 20 አገራት ማኅበር አባል ደቡብ አፍሪካ ብቻ ነች። በአፍሪካ ኅብረት 55 አባል አገራት ይገኛሉ።

ባለፈው ነሐሴ ዩናይትድ ስቴትስ ከሰሃራ ግርጌ የሚገኙ አገሮችን በተመለከተ አዲስ ስልታዊ ሰነድ አውጥታለች። ይህም የቀጠናውን አስፈላጊነት፣ በቻይናና በሩሲያ የተጋረጠውን አደጋ፣ እንዲሁም ተመሳሳይ አስተሳሰብ ካላቸው አገራት ጋር ወታደራዊ ትብብር ማድረግን የተመለከተ ነው።

“አፍሪካን ለመርዳት ነገሮችን በአዲስ መልክ ማከናወን እንደሚያስፈልግና፣ አፍሪካን እንደ የጂኦ-ፖለቲካ ስትራቴጂ አጋር ሳይሆን፣ በራሷ እንደ ዋና ተዋናይ መቁጠር” እንደሚይስፈልግ የዩናይትድ ስቴትሱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ባለፈው ወር ተናግረው እንደነበር የሮይተርስ ዘገባ አስታውሷል።

ለመንገድና ባቡር መሥመር ግንባታ፣ ለግድብ እና ሃይል ማመንጫ እንዲሁም ለሌሎችም ግንባታዎች አፍሪካ በዓመት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ያስፈልጋታል። ባለፉት አስር ዓመታት ከቻይና ዳጎስ ያለ ገንዘብ ለዚሁ ጉዳይ አግኝታለች።

ዋሽንግተን የቻይናን ብድር እንደ “ወጥመድ” ትቆጥረዋለች። አህጉሪቱን በእዳ የሚዘፍቅ ነውም ትላላች። በተቃራኒው በግል ለሚደረግ ኢንቨስትመንት ድጋፍ ማድረግ ላይ ትኩረት አድርጋለች። ባለሥልጣናት እንደሚሉት ግን፣ ድጋፉን ለማጠናከር ብዙ ማድረግ ይጠበቅባታል።

የባይደን አስተዳደር ለአፍሪካ ትኩረት አይሰጥም በሚል ትችት ይቀርብበታል። የቻይና የፖለቲካና የኢኮኖሚ ትብብር አህጉሪቱ ላይ በጥልቀት ሥር እየሰደደ ባለበት በዚህ ወቅት ትችቱ ይበልጥ በመሰማት ላይ ነው ብሏል ሮይተርስ በዘገባው።

በሌላ በኩል የቪኦኤዋ ዘጋቢ ማሪያማ ዲያሎ በዋሽንግተን የአፍሪካ ዲፕሎማቲክ ቡድን ዲን ከሆኑት የኮንጎ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሰርጅ ሙዬ ጋር ባደረገችው ቆይታ ከዋይት ሃውስና ከውጪ ጕዳይ ሚኒስቴር መ/ቤቱ ጋር ለወራት ለቆየ ግዜ ለጉባኤው ዝግጅት እንደሰሩ አጫውተዋታል።

“መጀመሪያ የምንጠብቀው የአፍሪካ አገሮች በተናጠል ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር እንዲያጠናክሩ፤ ከዛም በአህጉር ደረጃ በአፍሪካና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል ትብብሩ እንዲጠናከር ነው። ይህ ጉባኤ ለአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 ስኬታማነት ዩናይትድ ስቴትስ አስተዋጽኦ የምታደርግበት እንዲሆንም እንፈልጋለን” ብለዋል ሰርጅ ሙዬ ከጉባኤው ስለሚጠብቁት ሲናገሩ።

የአፍሪካ ኅብረት እንደሚለው፣ አጀንዳ 2063 የተባለው ዕቅድ አፍሪካን በዓለም መድረክ ዋና ተዋናይ ለማድረግ ሁሉንም የሚያቅፍ ማህበረሰባዊ ዕድገትን፣ አህጉራዊ እና ቀጠናዊ ውህደትን፣ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን፣ እንዲሁም ሰላምና መረጋጋትን ቅድሚያ ሰጥቶ የሚንቀሳቀስ ዕቅድ ነው።

“እኛ አፍሪካውያን የኃይል አቅርቦት፣ መሠረተ ልማት፣ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጉናል። አፍሪካን ለማልማት መልካም ጤና ያስፈልገናል። በመሆኑም፣ ይህ ጉባኤ በተጠቀሱት መስኮች በአፍሪካና በዩናይትስ ስቴትስ መካከል ትብብር እንዲኖር አስተዋጽኦ ያደርጋል” ሲሉ ሰርጅ ሙዬ አክለዋል።

የቀድሞ ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ የመጀመሪያውን የዩኤስ-አፍሪካ መሪዎች ጉባኤ እ.አ.አ 2014፣ ከስምንት ዓመታት በፊት መሆኑ ነው፣ አዘጋጅተው ነበር። ከዛ ወዲህ ብዙ ነገሮች ተከስተዋል።

ጁዴ ሙር በዓለም አቀፍ ልማት ማዕከል ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። ጉባኤው የሚደረገው ወሳኝ በሆነ ወቅት ነው ይላሉ።

“በአፍሪካ አገሮች በኩል፣ ዩናይትድ ስቴትስ በአንዳንድ ጉዳዪች ላይ ለምሳሌ በዋጋ ግሽበት፣ በነዳጅ እጥረት፣ በዩክሬን ያለው ጦርነት በሰዎች ኑሮና ህይወት ላይ ስለሚያስከትለው ተጽእኖ እና በመሳሳሉ ጉዳዮች ላይ ያላትን አቋም እንድታሳወቅ ይጠብቃሉ። በተለይ ደግሞ ይህ ጉባኤ ከ ኮፕ 27 በኋላ እንደመደረጉ፣ የአፍሪካ መሪዎች ለከባቢ አየር ቀውስ የሚሰጠውን ምላሽ በተመለከተ ዩናይትድ ስቴትስ የመሪነት ሚና እንድትጫወት የጠብቃሉ” ብለዋል ጁዴ ሙር።

በተመድ የአፍሪካን አህጉር በተመለከተ ባለፈው ዓመት የወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከሌሎች አህጉሮች አንጻር የአፍሪካ አህጉር በይበልጥና በፍጥነት ሞቃታማ በመሆን ላይ ነው። ነገር ግን አፍሪካ ለአየር ብክለት ወይም ለግሪንሃውስ ጋዝ ብክለት ያላት አስተዋጽኦ 4 በመቶ ብቻ ነው።

ሰርጅ ሙዬ ስለ ኮንጎ ተፋሰስ ብሉ ፈንድ ያነሳሉ። ፈንዱ የአካባቢው አገሮች ደኑን ከመጉዳት እንዲቆጠቡ የሚያበረታታ ነው።

“በእኛ በኩል ምድርን ወይም ከባቢ አየርን ለመንከባከብ፣ ለምሳሌ በኮንጎ ተፋሰስ አካባቢ፣ ወይም በኮንጎ ተፋሰስ የሚገኘው ሰማያዊው ፈንድ በገንዘብ መደገፍ አለበት። በብዙ አገሮች ቃል ተገብቷል፣ ነገር ግን ዳጎስ ያለ የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ አይታዩም” ብለዋል ሰርጅ ሙዬ።

የኮንጎ ተፋሰስ እየተባለ የሚጠራው አካባቢ በዓለም ትልቁ ትሮፒካል ደን የሚገኝበት ሥፍራ ነው።

አፍሪካ በቅርቡ በርካታና ተደጋጋሚ መፈንቅለ-መንግስቶችን አስተናግዳለች። በተለይም በምዕራብ በሚገኙት ማሊ፣ ጊኒ እና ቡርኪና ፋሶ። እነዚህ አገሮች በጉባኤው ላይ ካልተጋበዙት አገሮች አንዳንዶቹ ናቸው።

“እጅግ አስቸጋሪ ወቅት ነው። የአፍሪካ መንግስታት የጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ ከዩናይትድ ስቴትስ የበለጠ ዕርዳታ ይጠብቃሉ፤ ምክንያቱም ማዕቀብ መጣል ስለምትችል። የሚጣለውን ቅጣት ማሳየት ብቻ ሳይሆን፣ ለመልካም ተግባር ማበረታቻ እነደሚሰጥ ማሳየት አለባት። በአብዛኛው እንደምነየው ግን ተቋሞቹ ማበረታቻውን ለመሰጠት በቂ ሃብት የላቸውም።”

ጉባኤው ነገ ማክሰኞ ተጀምሮ፣ ሐሙስ ይጠናቀቃለ ተብሎ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአሜሪካ የሚገኙ የተለያዩ ማኅበራትና ግለሰቦች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ይካሄዳል ያሉትን ሁከት በመጥቀስ ፕሬዝደንት ባይደን የኢትዮጵያን ፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴን ለጉባኤው መጋበዛቸውን በመቃወም ደብዳቤ ጽፈዋል፣ ግብዣው አንዲሰረዝም ጥሪ አድርገዋል።

የኦሮሞ ቅርስ የአመራርና የመብት ተሟጋች ማኅበር የተሰኘው አካል ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሚያ ክልልና በሰሜን ኢትዮጵያ ይፈጸማል ያለውን ሁከት በመጥቀስ የአሜሪካ ባለስልጣናት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ከፕሬዝደንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ጋር የመገናኘታቸውን ጉዳይ “መልሰው እንዲያጤኑትና ከኦሮሞ ህዝብ ጎን እንዲቆሙ” ጥሪ አድርጓል።

በተመሳሳይ 21 የሚሆኑ ድርጅቶችና 17 የሚሆኑ ግለሰቦች ለፕሬዝደንት ጆ ባይደን በጻፉት ደብዳቤ፣ በኦሮሚያና በቤኒ ሻንጉል ክልል በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ይካሄዳል ባሉት “ጭፍጨፋና የሰባዓዊ መብት ረገጣ” ምክንያት ለፕሬዝደንት ሳህለወርቅ ዘውዴም ሆነ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስተዳደር በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ የቀረበላቸው ግብዣ እንስዲሳብ ጥሪ አድርገዋል።

በደብዳቤያቸው፣ “የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አመራር ወቅት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙትን ወጀሎች ያውቃል” ያሉት ድርጅቶቹና ግለሰቦቹ፣ “ጨካኝ” ብለው ከገለጹት መንግሥት መሪዎች ጋር “አብሮ መብላትና መጠጣት ተግባራቸውን መደገፍ ማለት ነው” ሲሉ አክለዋል።

XS
SM
MD
LG