በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአውሮፓ ህብረት ሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ለመጣል እየተነጋገረ ነው


ፋይል - ከላይ የሚታየው የዩክሬን ባንድራ ከሌሎች የአውሮፓ ባንድራዎች ጋር ከአውሮፓ ፓርላማ ውጪ ሲውለበለብ
ፋይል - ከላይ የሚታየው የዩክሬን ባንድራ ከሌሎች የአውሮፓ ባንድራዎች ጋር ከአውሮፓ ፓርላማ ውጪ ሲውለበለብ

የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገሮች የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ሩሲያ ላይ ተጫማሪ ማዕቀብ ለመጣል ውይይት ላይ ናቸው። ለዩክሬን የጦር ኃይል በሚላክ ተጨማሪ የገንዘብ ዕርዳታ ላይም እየመከሩ መሆናቸው ተዘግቧል።

ሩሲያ ወሳኝ የሆኑ የዩክሬን መሰረተ ልማት አውታሮችን በአየር ማጥቃቷን በቀጠለችበት ባሁኑ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬንን መርዳቷን እንደምትቀጥል ቃል ገብታለች።

የአውሮፓ ህብረት ብራሰልስ ውስጥ ዩክሬን ለጦር መሳሪያ አቅርቦት መግዣ የምታውለው 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት እንደሆነ ተመልክቷል።

አህጉራዊው ህብረት የሩሲያን ወረራ ተከትሎ በግለሰቦች እና ኢንዱስትሪዎቿ ላይ ስምንት ዙር ማዕቀብ የደነገገ ሲሆን ዘጠነኛው ዙር ማዕቀብ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ የመከላከያ እና የባንክ ኢንዱስትሪዋ ላይ እንደሚያነጣጥር ተጠቁሟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ትናንት ዕሁድ የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪን በስልክ አነጋግረዋል። ዜሌንስኪ በዚህ ሳምንት የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎችም ቁልፍ ጉባዔዎች ከመካሄዳቸው አስቀድሞ የአለም መሪዎችን በማነጋገር ላይ ናቸው።

ፕሬዚደንት ባይደን ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የጸጥታ፥ የኢኮኖሚ እና የሰብዐዊ ረድዔት ድጋፍ ማድረጓን እንደምትቀጥል ለዜሌንስኪ በድጋሚ ያረጋገጡላቸው መሆኑን የኋይት ሐውስ መግለጫ አውስቷል። ሩሲያን በምትፈጽመው የጦር ወንጀል እና በጭካኔ አድራጎቶቿ ተጠያቂ ማደረጋችንን እና መቅጣታችንን እንቀጥላለን ማለታቸውንም መግለጫው አክሏል።

የፈረንሳይ ፕሬዚደንት ኢማኑዌል ማክሮንም የዩክሬንን ፕሬዚደንት ያነጋገሩ ሲሆን "የወሰደውንም ጊዜ ይውሰድ ዩክሬን ሉዐላዊነቷን እና የግዛት አንድነቷን መልሳ እስከምታስከብር ድረስ ፈረንሳይ መርዳቷን እንደምትቀጥል አረጋግጥሎታለሁ" ብለዋቸዋል።

ፕሬዚደንት ዜሌንስኪ አገራቸው በሶስት ወደቦች በኩል የዕህል አቅርቦት ለማስወጣት ያስቻላት የጥቁር ባህር የእህል አቅርቦት መርሃ ግብር መስፋፋት ስለሚቻልበት መንገድ ከቱርክ ፕሬዚደንት ሬቼፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር መነጋገራቸውን አስታውቀዋል።

XS
SM
MD
LG