በሩሲያ እየተካሄደ ያለው ጦርነት፣ በሄይቲ ያለው ቀውስና በሜክሲኮ ያሉ ወንጀለኛ ቡድኖች በዓለም ዙሪያ በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጸመውን ግድያ 30 በመቶ እንዲጨምር አድርጓል ሲል ዛሬ የወጣ ሪፖርት ይፋ አድርጓል።
ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን የተሰኘው ተቋም ባወጣው ሪፖርት መሠረት እየተጠናቀቀ ባለው በዚህ የፈረንጆች ዓመት 67 ጋዜጠኞችና የመገናኛ ብዙሃን ሠራተኞች በዓለም ዙሪያ ተገድለዋል። ይህም ባለፈው ዓመት ከነበረው 47 የጋዜጠኞች ሞት ጭማሪ ያሳየ ነው።
መሠረቱን በብራስልስ ያደረገው የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን እንዳለው በዓለም ዙሪያ በአሁኑ ወቅት 375 ጋዜጠኞች በሥራቸው ምክንያት ታሥረው ይገኛሉ። ባለፈው ዓመት በእስር ላይ የነበሩት ጋዜጠኞች ቁጥር 365 ነበር።
የጋዜጠኞች ግድያ እየጨመረ ባለበት በዚህ ወቅት፣ መንግስታት ጋዜጠኞችን በመከላከል ረገድ እርምጃ እንዲወስዱና ጋዜጠኝነትንም ነጻ እንዲያደርጉ ፌዴሬሽኑ ጥሪ አድርጓል።
በዚህ ዓመት አብዛኞቹ ጋዜጠኞች የሞቱት የዩክሬኑን ጦርነት በመዘገብ ላይ ሳሉ እንደሆንና ቁጥራቸውም 12 እንደሆነ የፈዴሬሽኑ ሪፖርት አመልክቷል ሲል አሶስዬትድ ፕረስ ዘግቧል።
የወንጀል ቡድኖች በሜክሲኮ መበራከትና በሄይቲ የሕግና ሥርዓት መፍረስ የጋዜጠኞችን ሞት እንዲጨምር አድርጓል ብሏል ፊዴሬሽኑ። ሜክሲኮ አሁንም ለጋዜጠኞች አደገኛ ቦታ ናት ተብሏል።
መሠረቱን በብራስልስ ያደረገው ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን በ140 አገራት ያሉ 600ሺህ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ይወክላል።