ኢራን በመካሄድ ላይ ባለው ፀረ-መንግስት ተቃውሞ ተሳትፎ ነበር የተባለን ግለሠብ በስቅላት መቅጣትዋን ዛሬ አስታውቃለች።
ሞሸን ሸካሪ የተባለው የ 23 ዓመት ወጣት ዛሬ ሐሙስ ጠዋት በስቅላት መገደሉን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል። ወጣቱ መንገድ በመዝጋትና አንድ የፀጥታ ኃይል አባልን በማጥቃት ክስ ቀቦበት ነበር።
የኢራን ፍ/ቤቶች 10 ሰዎችን በፀረ-መንግስት ተቃውሞ ላይ በመስተፋቸው በሞት እንዲቀጡ የወሰኑ ሲሆን የሞሸን ሸካሪ የስቅላት ቅጣት የመጀመሪያው መሆኑ ነው የተገለፀው።
“በኢራን የሰብዓዊ መብት ዘመቻ” የተሰኘው ቡድን ሃላፊ የሆኑት ሃዲ ጋሄሚ ለአሜሪካ ድምፅ የፐርሽያ አገልግሎት ሲናገሩ “በኢራን ፍ/ቤቶች የሚተላለፉት ሁሉም የሞት ቅጣቶች ፖለቲካዊ ናቸው” ብለዋል።
ማሻ አሚኒ የተባለች ከኩርድ ወገን የሆነች ኢራናዊ ባለፈው መስከረም ሂጃብ በትክክል አልለብሽም በሚል በፀጥታ አስከባሪዎች ከተያዘች በኋላ ህይወቷ በማለፉ በኢራን ከፍተኛ የፀረ-መንግስት ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አሊ ኻመኒ እህት በተቃዋሚዎች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት አውግዘው የኢራን አብዮታዊ ዘብ ከድርጊቱ እንዲቆጠብ ጠይቀዋል።
ልጃቸው በፈርንሳይ ይፋ አድርጎታል በተባለ ደብዳቤ፣ በኢራን የሚኖሩት የመንፈሳዊው መሪ እህት ባርዲ ኻሚኒ፣ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገውን የኢስላሚክ ሪፐብሊክ ከምሥረታው እስከ አሁን ያለውን ሂደት ተችተዋል።
ደብዳቤውን ይፋ ያደረገው ልጃቸው ሞራድካኒ፣ እርሱም ሆነ እናቱ ከመንፈሳዊው መሪ ካሚኒ ጋር ላለፉት 13 ዓመታት ተገናኝተው እንደማያውቁና ከጅምሩ አንስቶ እናቱ አገዛዙን እንደማይደግፉ አስታውቋል።