በደቡብ ሱዳን ሰሜናዊ ክፍል የሚታየውን ሁከት ለመሸሽ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ባለፉት ሣምንታት መኖሪያቸውን ጥለው ወጥተዋል ሲሉ በአካባቢው የሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ወኪሎች አስታውቀዋል። አንዳንዶቹ በአካባቢው ባለ ቁጥቋጦ ተደብቀው ህይወታቸውን ለማቆየት ቅጠላ ቅጠል ለመመገብ ተገደዋል ተብሏል።
የላይኛው ናይል እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ የሚታየው ደም መፋሰስ በቁጥር በውል የማይታወቁ ሰዎችን ህይወት እንደቀጠፈና አስገድዶ መድፈር እና የሲቪሎች መታገት እየጨመረ ነው ተብሏል።
የተባበሩት መንግስት ድርጅት የሰብዓዊ ሥራዎች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) እንዳለው ባለፈው ወር አጋማሽ ላይ በታጣቂ ቡድኖች መካከል ግጭት ሲጀመር፣ ፋሾዳ ከምትባለውና በላይኛው ናይል ከምትገኘው አውራጃ 9ሺህ 100 ሰዎች ተፈናቅለዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች መርጃ ድርጅት (ዩ.ኤን.ኤች.ሲ.አር) በበኩሉ ግጭቱ ከጀመረበት ካለፈው ነሃሴ ጀምሮ 20 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች ሲፈናቀሉ ከነዚህ ውስት 3 ሺህ የሚሆኑት ድንበር አቋርጠው ወደ ጎረቤት ሱዳን ዘልቀዋል።
ማላካል በተሰኘ ሥፍራ የተቋቋመው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ካምፕ 12 ሺህ ሰዎች ለመያዝ የተሰራ ቢሆንም 37 ሺህ ተፈናቃዮችን ለማስተናገድ ተገዷል።