በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከዩክሬን ወደ ኢትዮጵያ የተላከ 25 ሺህ ቶን ስንዴ ጂቡቲ ወደብ ደርሷል


ፋይል - እ.አ.አ ነሐሴ 3፣ 2022 ዓ.ም ኤም ቪ ብሬቭ ኮማንደር የተሰኘው መርከብ ከዩክሬን ዩዝኒ ወደብ ተነስቶ ጅቡቲ ሲደርስ
ፋይል - እ.አ.አ ነሐሴ 3፣ 2022 ዓ.ም ኤም ቪ ብሬቭ ኮማንደር የተሰኘው መርከብ ከዩክሬን ዩዝኒ ወደብ ተነስቶ ጅቡቲ ሲደርስ

ከዩክሬን ወደ ኢትዮጵያ የተላከ 25 ሺህ ቶን ስንዴ ባለፈው ቅዳሜ በጂቡቲ ዶራሌ ወደብ ደርሷል ሲሉ የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ አስታውቀዋል። ይህም በድርቅና ቸነፈር ለተጠቁ አገሮች ምግብ ለመላክ የሚደርገው ጥረት አካል መሆኑን ገልፀዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ 25 ሺ ቶን የሚመዝነው ስንዴ በዓለም የምግብ ፕሮግራም በኩል ከሚላከው ውጪ መሆኑን ማረጋገጡን አሶስዬትድ ፕረስ ዘግቧል።

ወደ ኢትዮጵያ የሚያመራ ሌላ 30 ሺህ ቶን የሚይዝ መርከብ በሚቀጥለው ሳምንት እንደሚነሳና፣ ወደ ሶማሊያ የሚላክ ሌላ ሶስተኛ መርከብ ደግሞ 25 ሺህ ቶን ስንዴ እየተጫነበት እንደሆነ ኤምባሲው ገልጿል።

ዩክሬንና ሌሎች ሸሪኮቿ የሆኑ አገሮች 150 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ ስንዴ ወደ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያ፣ ኮንጎ፣ ኬንያ እና የመን ለመላክ ከሳምንት በፊት ተስማማተው ነበር።

“ምግብ እንልካለን፣ ተስፋን እንልካለን” ሲሉ በትዊተር መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ዜሌንስኪ 25ሺህ ቶን ስንዴ የያዘው መርከብ ጂቡቲ ዶራሌ ወደብ ሲደርስ የሚያሳይ ቪዲዮም ከመለዕክታቸው ጋር አጋርተዋል።


ዜሌንስኪ ባለፈው ዓርብ እንዳስታወቁት በመጪው የፈረንጆች ዓመት መጀመሪያ ላይ 60 መርከቦች ለተጠቀሱት አካባባኢዎች ጭነት ያደርሳሉ።


አምስት የዝናብ ወቅቶች በተከታታይ ደረቅ ሆነው ካለፉ በኋላ፣ በኢትዮጵያ ሶማሊያ እና ኬንያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በቸነፈር ተመተዋል። በኢትዮጵያና ሶማሊያ የሚካሄዱ ግጭቶች ደግሞ ችግሩን አባብሰውታል።

ከዩክሬን የተላከውን ስንዴ በተመለከተ ኢትዮጵያ እስካሁን ያለችው የለም። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከዩክሬን ወደ ኢትዮጵያ ስንዴ የመላኩን ጥረት በተመለከተ ግን ባለፈው ነሐሴ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ሲናገሩ፣ “እንደተራብን አድርገው ለማቅረብ” የሚያደርጉት ጥረት ነው ሲሉ መተቸታቸው ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG