የኡጋንዳ ባለስልጣናት ባለፉት አስር ቀናት ውስጥ አዲስ የኢቦላ ቫይረስ ኢንፌክሽን አለመከሰቱን ቢያስታውቁም፣ ሀገሪቱ የቫይረሱን ስርጭት ለመገደብ፣ ትምህርት ቤቶች ለገና በዓል ከሚዘጉበት ሁለት ሳምንት ቀድመው እንዲዘጉ ወስናለች።
አርብ እለት ሁሉም በኡጋንዳ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎች ወደየቤታቸው እንዲመለሱ ያደረጉ ሲሆን መንግስት ውሳኔውን ያሳለፈው በሀገሪቱ የ55 ሰዎችን ህይወት የቀጠፈውን የኢቦላ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር መሆኑን ገልጿል። በኡጋንዳ ጤና ሚኒስትር የክስተት አዛዥ የሆኑት ሉተናንት ኮሎኔል ሄነሪ ኪዮቤ ለአሜሪካ ድምፅ በስልክ ሲናገሩ ሀገሪቱ አሁን ያለችበት ሁኔታ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም የሚወሰዱ ጥንቃቄዎች ግን በከፍተኛ ሁኔታ መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ኪዮቤ እንዳሉት ሀገሪቱ ከኢቦላ ቫይረስ ስጋት ነፃ መሆኗ የሚረጋገጠው የመጨረሻው ተጠቂ ከተገኘበት ግዜ አንስቶ ሁለት የቫይረሱ መራቢያ ዑደቶች ካለፉ በኃላ ነው። አክለውም ላለፉት ሰባት ቀናት ባለስልጣናት 4ሺህ 473 ንክኪ የነበራቸው ሰዎች ላይ ክትትል መደረጉን ጠቅሰው አሁን ቁጥሩ ወደ 200 መውረዱን ተናግረዋል።
በኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ወደ ኡጋንዳ የሚጓዙ ጎብኚዎች ቁጥር በከፍተኛ የቀነሰ ሲሆን የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቨኒ ባለፈው ሳምንት ለሀገራቸው ህዝብ ባደረጉት ንግግር ቱሪውቶች ጉዟቸውን መሰረዛቸው አላስፈላጊ ነው ብለዋል።
እስከጥቅምት መጨረሻ ባለው ጊዜ ድረስ ኡጋንዳ ገዳይ በሆነውና የሱዳን ዝርያ በመባል የሚታወቀው የኢቦላ ቫይረስ የተጠቁ 141 ሰዎች መኖራቸውን አረጋግጣለች።