የምሥጋና ቀን በማስመልከት በየዓመቱ የሚካሄደው ‘የሜሲስ የምሥጋና ቀን ሰልፍ’ በኒው ዮርክ ከተማ በደማቁ ተከናውኗል።
ለ96ኛ ዓመት የተካሄደውን ሠልፍ ለመመልከት በርካታ ሰዎች የኒው ዮርክን አውራ ጎዳና ሞልተው ውለዋል።
መቶ ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሠልፍ ሥነ-ሥርዓት ትናንት ሲካሄድ በአየር የተነፉ አሻንጉሊቶችና ተሽከርካሪዎች የተለያዩ ትርዒቶችን አሳይተዋል።
ሴንትራል ፓርክ ተብሎ ከሚጠራው በከተማው መካከል ከሚገኝ መናፈሻ እስከ ሄራልድ አደባባይ ድረስ 40 መታጠፊያዎችን የሸፈነ ሠልፍ ነበር።
በበዓሉ ዕለት በሌሎች የአሜሪካ ከተሞችም ሠልፍ የሚካሄድ ሲሆን፣ የኒው ዮርኩ ሠልፍ ግን የምሥጋናው ቀን ምልክት ተደርጎ የሚቆጠርና ከመላው አሜሪካ የሚመጡ ጎብኚዎች የሚሳተፉበት ነው። 50 ሚሊዮን የሚሆኑ አሜሪካውያን ደግሞ ሠልፉን በቴሌቭዝን መስኮት ይመልከታሉ።
እአአ በ1863 የወቅቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት አብረሃም ሊንከን፣ በህዳር ወር የመጨረሻው ሐሙስ የምስጋና ቀን እንዲሆንና የሃገሪቱ ዜጎች ስለተሰበሰበው የእህል ምርት ለአምላካቸው ምስጋና እንዲያቀርቡና በይፋ ደንግገዋል።