በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በምዕራብ ኦሮምያ የፀጥታና ደኅንነት ችግር እንደቀጠለ ነው


በምዕራብ ኦሮምያ የፀጥታና ደኅንነት ችግር እንደቀጠለ ነው
please wait

No media source currently available

0:00 0:11:45 0:00

በኦሮምያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ውስጥ ታጣቂዎች ባለፈው አርብ ጥቃት አድርሰው ሰላማዊ ሰዎችና የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎችን ገድለዋል ሲሉ ነዋሪዎች እንደሆኑ የገለፁ ሰዎች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

ቃላቸውን ለቪኦኤ የሰጡ እማኞች መሆናቸውን የጠቆሙ ነዋሪዎች ለተፈፀሙት ግድያዎች በአንድ ወገን “የአማራ ፅንፈኞች” የሚሏቸውን ታጣቂዎች ሲወነጅሉ በሌላው ደግሞ “የኦሮምያ ልዩ ኃይል አባላት”ና "ሸኔ" ሲሉ የጠሯቸው ታጣቂዎች ብዙ ሲቪሎችን መግደላቸውን ገልፀዋል።

በተመሳሳይ ዜና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ አሊቦ ከተማ ውስጥም ባለፈው ሳምንት "የአማራ ፅንፈኞች ናቸው" ያሏቸው ታጣቂዎች “ብዙ ሰው ገድለዋል፤ ቤትና ንብረት አቃጥለዋል” ሲሉ ከአካባቢው ተፈናቅለው ሻምቡ ከተማ እንደሚገኙ የተናገሩ ግለሰብ በስልክ በሰጡት ቃል አመልክተዋል።

በሌላ በኩል “ፅንፈኞችና ፋኖ የሚሉት ጥቃት ሲፈፀምበት እራሱን የሚከላከለውን ነዋሪ ነው” ያሉ ተፈናቅለው ሃሮ ውስጥ እንዳሉ በስልክ የጠቆሙ አንድ የኪረሙ ነዋሪ ውጥረቶችን በሽምግልና ለማርገብና እርቅ ለማውረድ የተጀመረ ጥረትም ድንገት በተነሣ ሁከት መስተጓጎሉን ገልፀዋል።

አንዳንድ የአካባቢው የጤና ባለሥልጣናት የቆሰሉ ሰዎች ለህክምና ወደ እነርሱ ሄደው እንደነበረ ቢያረጋግጡም አስከሬኖች እንዳልደረሷቸውና ተገደሉ ስለተባሉ ሰዎች የተጨበጠ መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

የኦሮሞም የአማራም ተወላጆች ከኪረሙ ተፈናቅለው በተለያዩ አካባቢዎች ችግር ውስጥ እንደሚገኙና በአካባቢው በቂ የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች እንደሌሉ ለቪኦኤ ገልፀዋል።

ባለሥልጣናቱ “ሸኔ” የሚሏቸው “የኦሮሞ ነፃነት ጦር” ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል "በአካባቢው ንፁሃን ዜጎችን ለመግደል በሚንቀሳቀስ ኃይል ላይ እርምጃ ወስደናል” ብለዋል። ይሁን እንጂ ታጣቂዎቻቸው ሰላማዊ ሲቪሎች ላይ ግድያ አለመፈፀማቸውን ተናግረዋል።

ከወረዳዎቹ አንስቶ እስከ ዞን ያሉ የአስተዳደርና የፀጥታ ባለሥልጣናትን በየእጅ ስልኮቻቸው ላይ በቀጥታ እየደወልን ለማግኘትና ሁኔታዎችን ለማጣራት፣ ምላሾቻቸውንም ለማካተት ለቀናት ያደረግናቸው ጥረቶች አልተሳኩም።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ደግሞ "አሁን ካለው የፀጥታ ሁኔታ አንፃር ወደ ሥፍራው መሄድ ባለመቻላችን በርቀት መረጃ እያሰባሰብን ነው" የሚል ምላሽ ለቪኦኤ ሰጥቶ "መረጃው ተሰባስቦ ሳያልቅ ምንም መናገር አንችልም" ብሏል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ በጉዳዩ ላይ የደረሰው ሪፖርት ወይም የሚያውቀው ዝርዝር እንዳለ ለመጠየቅ ጥረት አድርገናል። ዳይሬክተሩ ስልክ አላነሱም፤ ለአጭር የፅሁፍ መልዕክታችንም መልስ አልሰጡም።

ምዕራብ ኦሮምያ ውስጥ ላለፉት አራት ዓመታት በሸማቂዎችና መንግሥት ኃይሎች መካከል የተካሄዱ ግጭቶች የአካባቢውን ነዋሪዎች የሰላም እጦትና የደኅንነት ሥጋት ውስጥ መጣላቸውንና ቁጥሩ የበዛ ሰላማዊ ዜጋ መገደሉን፣ በመቶ ሺሆች የሚቆጠር ሰው መፈናቀሉን ስንዘግብ የቆየን ሲሆን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም በተለያዩ ጊዜዎች ባወጣቸው መግለጫዎች ምዕራብ ኦሮምያ ውስጥ ያለው የፀጥታ ችግር ትኩረት እንዲሰጠው በተደጋጋሚ ማሳሰቡ ይታወቃል።

ዘጋቢዎቻችን ሁኔታዎችን በንቃት እየተከታተሉ ነው። ከተጎጂዎች፣ ከተፈናቃዮች፣ ከእማኞች፣ በሁሉም ደረጃዎች ካሉ ባለሥልጣናት፣ ከተንታኞች ተሟጋቾችና ከሁሉም ወገኖች፣ ከሌሎችም ያገኘናቸውንና የምናገኛቸውን መረጃዎችና ቃሎች ዘርዘር ባሉ ዘገባዎች እየያዝን እንመለሳለን።

በሌላ በኩል ሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን ግጭት ለማስቆም በኢትዮጵያ መንግሥትና በህወሃት መካከል የሰላም ስምምነት ቢደረግም በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚካሄዱ ብሄር ተኮር ግጭቶች እና ጥቃቶች ግን አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው። እነዚህ ግጭቶች በዘላቂነት እንዴት ማስቆም ይቻላል? በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ ያለፉ ሃገሮች ተሞክሮስ ምን ይመስላል? በቺካጎ ዩንቨርስቲ መምህርና በምስራቅ አፍሪካ የተካሄዱ የብሄር ግጭቶች ያጠኑት ፕሮፌሰር አታናስ ጋሁንጉን አነጋግረናል።

/ሙሉውን ከተያያዘው ዘገባ ይከታተሉ/

XS
SM
MD
LG